ቀጥታ፡

መንግስት የተረሱና የተደበቁ እምቅ ጸጋዎችን በማልማት ሀገር እንድታንሰራራ እያደረገ ነው

አዳማ ፤ ጥቅምት 13/2018(ኢዜአ)፦መንግስት የተረሱና የተደበቁ የኢትዮጵያን እምቅ ጸጋዎች በማልማት የሀገርን ማንሰራራት እያስቀጠለ መሆኑን የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።

የኢትዮጵያ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ሃብቶች በሁሉም አካባቢዎች ያልተጠቀምንባቸውና እያየናቸው የምናልፋቸው እምቅ ሃብቶች ሆነው ተዘንግተው ቢኖሩም አሁን ላይ ግን መልማትና ጥቅም ላይ መዋል ጀምረዋል። 


 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰሞኑን በባሌ ዞን በነበራቸው ጉብኝትም ''የጋራ ሥራችን እነዚህን ኃብቶቻችንን መግለጥ፣ ማሳደግ፣ በኃብቶቹ ላይ በመጨመር ቀጣዩ ትውልድ ችቦውን ተረክቦ እንዲቀጥል መሠረት መጣል ነው'' በማለት መናገራቸው ይታወሳል።

በተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችንና የቀጣይ ሀገራዊ ተስፋዎችን በተመለከተ ኢዜአ ከሃረማያ እና መቱ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጋር ቆይታ አድርጓል።

በሃረማያ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪ  ሙሐመድ ሀሰን (ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያ እምቅ ሃብቶች ለዘመናት የተረሱ፣ ተገልጠው ያልታዩ እና ያልተጠቀምንባቸው ናቸው ይላሉ።


 

ለዚህም በባሌ ዞን ሰሞኑን የተመለከትነው በዚህ ልክ ለምቶ ጥቅም ላይ ሳይውል በመቆየቱ ቁጭት የፈጠረ ቢሆንም የቀጣዩን ተስፋ በማየታቸን ደግሞ ተደስተናል ብለዋል።

በመሆኑም መንግስት  የተረሱና የተደበቁ የኢትዮጵያን እምቅ ጸጋዎችን በማልማት የሀገርን ማንሰራራት እያስቀጠለ መሆኑን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል ብለዋል።

የሀገር ሃብት እያለ አልምቶ ባለመጠቀም በድህነት መጠራት የሚያስቆጭና አንገት የሚያስደፋ በመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሁሉም አካባቢዎች ሃብቶችን እየገለጡ በመሆኑ ሊደነቁና ሊመሰገኑም ይገባል ብለዋል።

ከዚህም በመነሳት በየደረጃው ያሉ አመራሮች በየአካባቢያቸው ያሉ ሃብቶችን በመግለጥ ለህዝብና ለሀገር ጥቅም ማዋል እንዳለባቸው አንስተዋል።


 

የመቱ ዩኒቨርሲቲ መምህር ሳቢር ዘይኑ፤ የሶፍ ዑመርን ልማት ጨምሮ በወንጪ፣ ጎርጎራ፣ አዲስ አበባ እና ሌሎችም አካባቢዎች በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተከናወኑ የልማት ስራዎች ኢትዮጵያ በሁሉም መስኮች ከፍ ብላ እየተሰራች መሆኗን የሚያመላክቱ ናቸው ብለዋል።


 

የቱሪስት  ሀብቶችን በመግለጥ የዘርፉን  ሁለንተናዊ አቅም ለማሳደግ በመንግስት የሚደረገው ጥረት የሚደነቅና የሁላችንም ትብብርና እገዛ ሊታከልበት ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም