ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የባሕር በር መሻት እውነትን ፍትሃዊነትንና ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን መሰረት ያደረገ ነው

ሐረማያ፤ ጥቅምት 13/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የባሕር በር መሻት እውነትን ፍትሃዊነትንና ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን መሰረት ያደረገ መሆኑን በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪ መሀመድ ሀሰን (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት የባህር በር የህልውና ጉዳይ መሆኑን በጽኑ በማመንና ጠንካራ አቋም በመያዝ በዲፕሎማሲው ረገድ በስፋት እየሰራ መሆኑ ይታወቃል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪ መሀመድ ሀሰን (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ የባህር በር ያጣችበት መንገድ የሚያስቆጭ መሆኑን አንስተዋል።

በተሰራው ታሪካዊ ስህተት የባህር በር አልባ መሆኗ ከቁጭትም ባለፈ ብዙ ዋጋ ያስከፈላትና አሁንም የቀጠለ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም  የአሁኑ መንግስት ስብራቶችን ለመጠገንና የሀገርን ብሄራዊ ጥቅም ለማስከበር የባህር በር የህልውና ጉዳይ አድርጎ መያዙ ተገቢና ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ የባሕር በር መሻት እውነትን ፍትሃዊነትንና ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን መሰረት ያደረገ በመሆኑ የዲፕሎማሲ ጥረቱ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ማጣት ለከፍተኛ ወጪ ከመዳረጉም ባለፈ ከባህር በቅርብ ርቀት ላይ ሊቃጣባት የሚችልን የባህር ላይ ውንብድና እና ሌሎች ተያያዥ ስጋቶችን ለመመከት አዳጋች የሚያደርግባት መሆኑንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በታሪክ አጋጣሚ ያጣችውን የባህር በር እውነት የማስመለስ መብት አላት ያሉት ተመራማሪው፤ በዚህ ረገድ ህጉም ይደግፋታል ጥያቄውም አግባብነት ያለው ነው ሲሉ አብራርተዋል።

የዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብም የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት እንደሚገነዘብ አንስተው የዲፕሎማሲ ጥረቱ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም