የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳል

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 13/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሁለተኛ ሳምንት በመጀመሪያ ቀን ውሎ አራት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ኢትዮጵያ ቡና ከነገሌ አርሲ ጋር ከቀኑ 7 ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ቡናማዎቹ በመጀመሪያው ሳምንት በደርቢው ጨዋታ በቅዱስ ጊዮርጊስ 1 ለ 0 መሸነፋቸው የሚታወስ ነው።
አዲስ አዳጊው ነገሌ አርሲ በሊጉ የመክፈቻ መርሃ ግብር ከአርባምንጭ ከተማ ጋር አንድ አቻ ተለያይቷል።
ሁለቱ ክለቦች በሊጉ የመጀመሪያ ግንኙነታቸው ሶስት ነጥብ ለማግኘት ይጫወታሉ።
ከቀኑ 10 ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ሸገር ከተማ ከአዳማ ከተማ ይጫወታሉ።
አዲስ አዳጊው ሸገር ከተማ በመጀመሪያ ጨዋታ በኢትዮ ኤሌክትሪክ 1 ለ 0 የተሸነፈ ሲሆን አዳማ ከተማ ከኢትዮጵያ መድን ጋር ባደረገው ጨዋታ ያለ ግብ አቻ ተለያይቷል።
በተያያዘም በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ።
ከቀኑ 9 ሰዓት ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከፋሲል ከነማ ይጫወታሉ።
ወልዋሎ በመጀመሪያ ጨዋታው በሲዳማ ቡና የ4 ለ 1 ሽንፈት ያስተናገደ ሲሆን ፋሲል ከነማ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር አንድ አቻ ወጥቷል።
ሁለቱ ክለቦች በ2017 ዓ.ም የውድድር ዓመት በሊጉ ሁለት ጊዜ ተገናኝተው ፋሲል ከነማ ሁለቱንም ጨዋታዎች ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
ወላይታ ድቻ ከድሬዳዋ ከተማ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በመጀመሪያው ሳምንት ወላይታ በመቻል 1 ለ 0፣ ድሬዳዋ ከተማ በሀዋሳ ከተማ የ2 ለ 0 ሽንፈት አስተናግደዋል።
ቡድኖቹ በሊጉ የመጀመሪያ ድላቸውን ለማስመዝገብ ይጫወታሉ።