በምዕራብ ጎንደር ዞን በተያዘው በጀት ዓመት ከ24 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ጎንደር ዞን በተያዘው በጀት ዓመት ከ24 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር እየተሰራ ነው

ገንዳ ውኃ፤ ጥቅምት 13/2018 ዓ/ም (ኢዜአ):- በምዕራብ ጎንደር ዞን በተያዘው የበጀት ዓመት ከ24 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር የሚያስችል ተግባራዊ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ስራና ክህሎት መምሪያ አስታወቀ።
የመምሪያው ምክትል ኃላፊ አስፋው በሪሁን፤ በአካባቢው ለስራ ዕድል ፈጠራ አመቺ የሆኑ ፀጋዎችን በመለየት በኢንተርፕራይዝ የተደራጁ ወገኖች እንዲሰማሩ እየተደረገ እንደሚገኝ ለኢዜአ ተናግረዋል።
በዞኑ ስራ ፈላጊ ወገኖች በግንባታ፣ በአረንጓዴ ልማት፣ በእጣንና ሙጫ፣ በመስኖ ልማት፣ በእንስሳት ማድለብና እርባታን ጨምሮ በሌሎች ዘርፎች እንዲሰማሩ ሲደረግ መቆየቱን አውስተዋል።
በተያዘው በጀት ዓመትም ከ24 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር የሚያስችል ተግባራዊ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ ከስራ ዕድል ማመቻቸት ባሻገር የገበያ ትስስር፣ ቁጠባና ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ብድር የማመቻቸት ስራም ትኩረት መሰጠቱን አስረድተዋል።
በሩብ ዓመቱ ከተመሰረቱት 2 ሺህ 400 ኢንተርፕራይዞች ውስጥ 249 ለሚሆኑት ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ የገበያ ትስስር መፍጠር እንደተቻለም አንስተዋል።
በቀጣይም እቅዱን በተሟላ መንገድ ማሳካት ይቻል ዘንድ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ስራ በቅንጅት እየተከናወነ እንደሚገኝም አስረድተዋል።
በዞኑ ገንዳ ውኃ ከተማ የቀበሌ 01 ነዋሪው ወጣት አላምረው አዲሱ በሰጠው አስተያየት፤ ስምንት ሆነው በግንባታ ዘርፍ በመሰማራት ተጠቃሚ መሆን እንደጀመሩ ገልጿል።
በከተማው በተመቻቸላቸው የመሰረተ ልማት ግንባታ ላይ በመሳተፍ በሚያገኙት ገቢ ተጠቃሚ ከመሆን ባሻገር የሙያ አቅማቸውን ለማሳደግ ምቹ ሁኔታ እንደተፈጠረላቸው ተናግረዋል።
ወጣት ዓለም ሙላት በበኩሏ፤ ተደራጅተው በዶሮ እርባታ ዘርፍ በመሰማራት ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸውን ገልፃለች።
በተመቻቸላቸው ሼድ ዶሮና እንቁላልን በተመጣጣኝ ዋጋ ለአካባቢው ማህበረሰብ እያቀረቡ መሆኑን ጠቅሳለች።