በሻምፒዮንስ ሊጉ ተጠባቂ ጨዋታ ሪያል ማድሪድ ጁቬንቱስን አሸነፈ - ኢዜአ አማርኛ
በሻምፒዮንስ ሊጉ ተጠባቂ ጨዋታ ሪያል ማድሪድ ጁቬንቱስን አሸነፈ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 12/2018 (ኢዜአ)፦ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ መርሃ ግብር ሪያል ማድሪድ ጁቬንቱስን 1 ለ 0 አሸንፏል።
ማምሻውን በሳንቲያጎ በርናባው ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ጁድ ቤሊንግሃም በ57ኛው ደቂቃ የማሸነፊያውን ጎል አስቆጥሯል።
ውጤቱን ተከትሎ ሪያል ማድሪድ በሻምፒዮንስ ሊጉ ሶስተኛ ድሉን በማስመዝገብ ነጥቡን ወደ ዘጠኝ ከፍ አድርጓል።
ጁቬንቱስ በውድድሩ የመጀመሪያ ሽንፈቱን ያስተናገደ ሲሆን እስከ አሁን ያገኘው ሁለት ነጥብ ብቻ ነው።
በሌሎች ጨዋታዎች ቼልሲ አያክስ አምስተርዳምን 5 ለ 1 አሸንፏል።
ማርክ ጉዊ፣ ሞይሰስ ካይሴዶ እና ታይሪክ ጆርጅ በጨዋታ ኢንዞ ፈርናንዴዝ እና እስቴቫኦ ዊሊያን በፍጹም ቅጣት ምት ግቦቹን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
ዉት ዌግሆረስት በፍጹም ቅጣት ምት ለአያክስ ብቸኛውን ጎል አስቆጥሯል።
ኬኔት ቴይለር በ15ኛው ደቂቃ ከአያክስ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል።
ሊቨርፑል ወደ ጀርመን በማቅናት ባደረገው ጨዋታ ኢንትራክት ፍራንክፈርትን 5 ለ 1 አሸንፏል።
ሁጎ ኢኪቲኬ፣ ቨርጂል ቫን ዳይክ፣ ኢብራሂማ ኮናቴ፣ ኮዲ ጋፕኮ እና ዶምኒክ ስቦዝላይ ግቦቹን አስቆጥረዋል።
ራስመስ ክሪስታይንሰን ለፍራንክፈርት ብቸኛውን ጎል ከመረብ ጋር አገናኝቷል።
ባየር ሙኒክ በሃሪ ኬን፣ ሉዊስ ዲያዝ፣ ኒኮላስ ጃክሰን እና ሌናርት ካርል ግቦች ክለብ ብሩዥን 4 ለ 0 ረቷል።
ስፖርቲንግ ሊዝበን ማርሴይን 2 ለ 1 ሲያሸንፍ፣ ሞናኮ ከቶተንሃም ሆትስፐርስ እና አትላንታ ከስላቪያ ፕራግ ያደረጓቸው ጨዋታዎች ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል።
ዛሬ አስቀድመው በተደረጉ ጨዋታዎች አትሌቲኮ ቢልባኦ ካራባግን፣ ጋላታሳራይ ቦዶ ግሊምትን በተመሳሳይ 3 ለ 1 አሸንፈዋል።