የዕጽዋት ጥበቃና ኳራንቲን ረቀቂ አዋጅ ኢትዮጵያ ያላትን የዕጽዋት ሀብት ዘመኑን በዋጀ መልኩ ለመንከባከብ አቅም ይፈጥራል - ኢዜአ አማርኛ
የዕጽዋት ጥበቃና ኳራንቲን ረቀቂ አዋጅ ኢትዮጵያ ያላትን የዕጽዋት ሀብት ዘመኑን በዋጀ መልኩ ለመንከባከብ አቅም ይፈጥራል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 12/2018(ኢዜአ)፦የዕጽዋት ጥበቃና ኳራንቲን ረቀቂ አዋጅ መዘጋጀት ኢትዮጵያ ያላትን የዕጽዋት ሀብት ዘመኑን በዋጀ መልኩ ለመንከባከብ አቅም እንደሚፈጥር በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሰለሞን ላሌ ገለጹ፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በዕጽዋት ጥበቃ እና ኳራንቲን ረቂቅ አዋጅ ላይ ከባለድርሻ አካላት የአስረጂ መድረክ አካሂዷል።
የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሰለሞን ላሌ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በዕጽዋት ሀብት የታደለች የበርካታ ብዝሀ ህይወት መገኛ ብትሆንም የተፈጥሮ ሀብቷን በአግባቡ መጠቀም የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ የላትም፡፡
ከዚህ በፊት የነበረው ህግ የግብርናን ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንቅፋት የሆነውን መጤና ወራሪ ተባይ ለመከላከል ውስንነት ነበረበት ብለዋል፡፡
በተለይም በዕጽዋት ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ ተባዮችን አስቀድሞ መከላከልና ጠንካራ የቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋት አያስችልም ነበር ነው ያሉት፡፡
በዚህም የዓለም አቀፍ የዕጽዋት ጥበቃ ስምምነትን መነሻ ያደረገ የዕጽዋት ጥበቃና ኳራንቲን ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ረቂቅ አዋጁ ኢትዮጵያ የዕጽዋት ሀብቶቿ ተገቢውን እንክብካቤ እንዲያገኙ እና መጤና ወራሪ ተባዮችን መከላከል የሚያስችል አቅም ይፈጥራል ብለዋል፡፡
ይሄውም ኢትዮጵያ በዓለም ገበያ ያላትን ተሳትፎ በማሳደግ ከዕጽዋት ዘርፍ የሚገባትን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንድታገኝ እንደሚያግዝ ገልጸዋል፡፡
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለሰ መኮንን (ዶ/ር)፤ መንግስት የግብርናን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የዕጽዋት ጥበቃና ኳራንቲን ረቀቂ አዋጅ ማዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡
ረቂቅ አዋጁ ትልቅ ለውጥ እንደሚያመጣ ገልጸው፤ ተባይ በዕጽዋት ላይ የሚያደርሰውን የምርት ብክነት መቀነስና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ማሳደግ ያስችላል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወንዳለ ሀብታሙ (ዶ/ር) በበኩላቸው ረቂቅ አዋጁ በዓለም አቀፍ ገበያ መወዳደር የሚያችሉ መስፈርቶችን የያዘ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዚህም ኢትዮጵያ ያላትን ዕምቅ የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ ጥቅም ለማዋል ወሳኝ ድርሻ ይኖረዋል ብለዋል፡፡