በአማራ ክልል የፍትህ አስተዳደር ሥርዓቱን ውጤታማ ለማድረግ የተጀመረው ቅንጅታዊ አሰራር ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የፍትህ አስተዳደር ሥርዓቱን ውጤታማ ለማድረግ የተጀመረው ቅንጅታዊ አሰራር ተጠናክሮ ይቀጥላል

ባህር ዳር፤ ጥቅምት 12/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የፍትህ አስተዳደር ሥርዓቱን ውጤታማ ለማድረግ የተጀመረው ቅንጅታዊ አሰራር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ፍትህ ቢሮ አስታወቀ።
የፍትህ ቢሮውና የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ በቅንጅት መስራት በሚያስችላቸው ተግባራት ላይ ያተኮረ የጋራ የትብብር ማዕቀፍ ሰነድ ዛሬ ተፈራርመዋል።
የክልሉ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ ብርሃኑ ጎሽም በመርሃ ግብሩ እንደገለጹት ወንጀሎችን ቀድሞ ለመከላከልና የፍትህ ስርዓቱን ለማዘመን በትኩረት እየተሰራ ነው።
የፍትህ ስርዓቱን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ ህብረተሰቡን በፍትሃዊነት ለማገልገል በቅንጅትና በትብበር መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።
ይህም በክልሉ ሰላም፣ ልማትና የህግ የበላይነትን በአስተማማኝ ሁኔታ በማረጋገጥ ጠንካራ የፍትህ ስርዓት በየደረጃው ለመገንባት ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።
የፍትህ ቢሮው እና የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ወንጀልን በመከላከል፣ ምርመራና ክስን በጥራትና በውጤታማነት በማከናወንና ሌሎች ስራዎችን በጋራ በመስራት ቅቡልነትን ማረጋገጥ ይገባል ነው ያሉት።
ይህም የሃብት ብክነትን በመቀነስ፣ ጉልበትና ጊዜን በመቆጠብ ስኬትን በጋራ ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ ገልጸው ዛሬ የተደረገው ስምምነትም ይህን የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ(ዶ/ር) በበኩላቸው እንደገለጹት አገልግሎትን ለማጠናከር የፍትህና የፖሊስ ተቋማት በጋራ ተናበው መስራት አስፈላጊ ነው።
የፖሊስና የፍትህ ተቋማት ተግባር የማይነጣጠሉ ናቸው ያሉት ኮሚሽነሩ ተቋማቱ ተቀናጅተውና ተናበው በመስራት የፍትህ አስተዳደር ስርዓቱን ማጠናከርና ውጤታማ ማድረግ አለባቸው ሲሉም አስገንዝበዋል።
በተዘጋጀው የጋራ የትብብርና የቅንጅት ማዕቀፍ ሰነድ የፊርማ ስነ-ስርዓት ላይ የሁለቱም ተቋማት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የመምሪያ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።