ቀጥታ፡

በባሌ ዞን የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን ስኬታማ ለማድረግ የውሃ መሳቢያ ፓምፕ ለአርሶ አደሮች እየተከፋፈለ ነው

ሮቤ፤ ጥቅምት 12/2018(ኢዜአ)፦ በባሌ ዞን የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን ለማሳካት የውሃ መሳቢያ ሞተር ፓምፖችን ለአርሶ አደሩ እያከፋፈለ መሆኑን የዞኑ የመስኖና አርብቶ አደር ልማት ጽህፈት ቤት ገለጸ። 

ጽህፈት ቤቱ በ53 ማህበራት ስር ለተደራጁ የሲናና ወረዳ አርሶ አደሮች የውኃ መሳቢያ የሞተር ፓምፖችን ዛሬ አከፋፍሏል። 


 

የዞኑ የመስኖና አርብቶ አደር ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አወል ኡመር በወቅቱ እንደገለጹት አርሶ አደሩ በአካባቢው የሚገኙ የውኃ አማራጮችን በአግባቡ በመጠቀም ውጤታማ እንዲሆን በትኩረት እየተሰራ ነው። 


 

በ2018 ዓ.ም በበጋ ወራት በዞኑ በሚገኙ 10 ወረዳዎች 183 ሺህ ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ እንደሚለማ ተናግረዋል። 

እንዲሁም የዞኑ አርሶና አርብቶ አደሮች ከሰብል ልማት በተጓዳኝ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት በመሰማራት በሚያገኙት ተጨማሪ ገቢ ውጤታማ እንዲሆኑ የሞተር ፓምፖቹ ትልቅ እገዛ እንደሚኖረቸው አክለዋል። 

እቅዱን ለማሳካት በማህበር ለተደራጁ የዞኑ አርሶ አደሮች 900 የውሃ መሳቢያ ሞተር ፓምፖችን የማከፋፋሉ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል። 

በሲናና ወረዳ በ53 ማህበር ለተደራጁ አርሶ አደሮች የተከፋፈሉ የውኃ መሳቢያ የሞተር ፓምፖች የዚሁ ጥረት አካል መሆኑን አስረድተዋል። 

አቶ አወል እንዳሉት በዞኑ የዛሬውን ጨምሮ ባለፉት የለውጥ ዓመታት 7 ሺህ የሚሆኑ የውኃ መሳቢያ ሞተር ፓምፖች ለአርሶ አደሮች የተሰራጩ ሲሆን እነዚህም ከ87 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ማልማት እንደሚችሉ አስታውሰዋል። 

የተሰራጩት የውሃ መሳቢያ ፓምፖች አርሶ አደሩ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን ጨምሮ በሌሎች ገበያ ተኮር የልማት ኢኒሼቲቮች ውጤታማ እንዲሆኑ እያገዙ መሆኑን ተናግረዋል። 

የሞተር ፓምፑን ከተረከቡ የሲናና ወረዳ አርሶ አደሮች መካከል ሐሰን ከድር በሰጡት አስተያየት የሞተር ፓምፑ በተለምዶ የሚያከናውኑትን የመስኖ ልማት ሥራ ለማዘመን እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል። 


 

የውሃ መሳቢያ ሞተሩ ከዚህ በፊት ያጋጥማቸው የነበረውን የውኃ ብክነትን በመቀነስ በዘርፉ ውጤታማ ለመሆን እንደሚያስችላቸው የገለጹት ደግሞ  የወረዳው አርሶ አደር ከተማ ፈይሳ ናቸው። 


 

አርሶ አደሮቹ የሞተር ፓምፑ በዓመት ሁለት ጊዜና ከዚያ በላይ በማልማት ውጤታማ ለመሆን እንደሚያግዛቸውም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም