ቀጥታ፡

የፍትህ ስርዓቱን ቀልጣፋ እና ተዓማኒ ለማድረግ የተጀመሩ ቅንጅታዊ አሰራሮችን ማጠናከር ይገባል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 12/2018(ኢዜአ)፦ የፍትህ ስርዓቱን ቀልጣፋ እና ተዓማኒ ለማድረግ የተጀመሩ ቅንጅታዊ አሰራሮችን ማጠናከር እንደሚገባ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።

ቋሚ ኮሚቴው የፍትህ ሚኒስቴርን የ2018 እቅድ እና የመጀመሪያ ሩብ ዓመት እቅድ አፈጻጸም ላይ ተወያይቷል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት የፍትህ ስርዓቱን ቀልጣፋ እና ተዓማኒ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተከናወኑ ያሉ ቅንጅታዊ አሰራሮችና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ምን ይመስላሉ ሲሉ ጠይቀዋል።

በማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ላይ የሚስተዋሉ ውስንነቶችን ፈጥኖ ለማረም እየተከናወኑ ስላሉ ስራዎችም ጥያቄ አቅርበዋል።

የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ ኤርሚያስ የማነብርሀን (ዶ/ር) በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ የፍትህ ስርዓቱን ቀልጣፋና ተአማኒነት የሚያረጋግጡ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውን ገልጸዋል።


 

በመጀመሪያው ሩብ ዓመት በህግ አወጣጥና ማሻሻያ ስራዎች እንዲሁም በመርታት ምጣኔ እና ፍርድን በማስፈጸም ውጤታማ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።

አጠቃላይ ስርዓቱን ተአማኒ ማድረግ የሚያስችል ዲጂታል አሰራር መዘርጋቱንም ነው ያብራሩት።

የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋዬ ዳባ በበኩላቸው እቅዱ በ2018 ለፍትህ እና ሰላም ዘርፍ የተሰጡ አቅጣጫዎችን ማእከል አድርጎ የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ከባለድርሻ አካላት ጋር በተከናወኑ ቅንጅታዊ አሰራሮች የተሻለ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን በመግለጽ።

በማረሚያ ቤቶች የሚስተዋሉ ውስንነቶችን መፍታት የሚያስችል ሀገር አቀፍ ጥናት እየተካሄደ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ በላይሁን ይርጋ ናቸው።

በተጨማሪም በርካታ ሰዎች ወደ ማረሚያ ቤት ከሚሄዱ ይልቅ ማህበረሰባዊ አገልግሎት የሚሰጡበትን ስርዓት የሚዘረጋ የአማራጭ ቅጣት ረቂቅ አዋጅ እየተዘጋጀ መሆኑን አንስተዋል።

የሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እጸገነት መንግስቱ የሚኒስቴሩ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ገልጸው ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።


 

በተቋማዊ አሰራርና አደረጃጀት ስራዎች ትምህርት የሚወሰድባቸው መሆናቸውን ጠቅሰው፥ በቀጣይም በዲጂታላይዜሽን ላይ የጀመራቸውን ስራዎች ወደ ክልሎች ማስፋት እንደሚገባ አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም