ቀጥታ፡

የወጣት ማዕከላትን የስብዕና ማበልፀጊያ በማድረግ የወጣቶችን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ  ነው

ባህር ዳር ፤ ጥቅምት 12/2018 (ኢዜአ)፦የወጣት ማዕከላትን የስብዕና ማበልፀጊያ በማድረግ የወጣቶችን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑን የኢፌዴሪ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የሚኒስቴሩ የወጣቶች ዘርፍ አመራሮችና የአማራ ክልል የስራ ሃላፊዎች በባህር ዳር ከተማ የሚገኙ የወጣት ማእከላትንና የባህርዳር ብሄራዊ ስታዲየምን ዛሬ ጎብኝተዋል።


 

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሙና አህመድ  በወቅቱ  እንደገለጹት በአገር አቀፍ ደረጃ ከ3ሺህ በላይ የወጣት ማዕከላት ይገኛሉ።

እነዚህ የወጣት ማእከላት የወጣቱን ስብእና በመገንባት ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት አብርክቶዋቸው በሚፈለገው ልክ አለመሆኑን በጥናት መለየቱን ተናግረዋል።

ይህን ችግርም በመቅረፍ ማእከላቱ በራሳቸው ገቢ በመተዳደር ለወጣቶች የመዝናኛና የማስተማሪያ አማራጭ በመሆን  መልካም ዜጋ ለመገንባት እንዲያግዙ  በአዲስ መልክ ለማደራጀት እየተሰራ ነው  ብለዋል።

በዚህም የወጣቶች ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ከማዘውተሪያነት ወደ ወጣት ስብዕና ማበልጸጊያነት ለማምጣት የሦስት ወር ንቅናቄ መጀመሩን ጠቁመው የአምስት ዓመት የስብእና ግንባታ ስትራቴጅ እየተዘጋጀ ነው ብለዋል።

ይህን ለማድረግም በባህር ዳር ከተማ የሚገኘው የሽምብጥ ሞዴል የወጣቶች ስብዕና ልማት ማዕከል በአሰራሩ፣ በአደረጃጀቱና ባለው ግብአት አርአያ በመሆኑ በተሞክሮነት ተወስዶ ወደ ሌሎች ለማስፋት እንደሚሰራ ገለጸዋል።


 

የአማራ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ እርዚቅ ኢሳ በበኩላቸው በክልሉ ከሚገኙት 466 የወጣት ማእከላት ውስጥ 280 የሚሆኑት አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በባህርዳር ከተማ የሚገኘው የሽምብጥ ሞዴል የወጣቶች ስብዕና ልማት ማዕከልም  ወጣቶችን ከማዝናናት ባለፈ የራሱን ገቢ በማመንጨት፣ በእርስ በእርስ መማማር፣ በስራ ፈጠራ ስልጠናና የምክር አገልግሎት በመስጠት አርአያ ነው ብለዋል።

በቀጣይም የማእከሉን ተሞክሮ ወደ ሌሎች በማስፋት የወጣቱን ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም