ቀጥታ፡

በጅማ ከተማ ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት በመስጠት ረገድ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት አበረታች ናቸው - ሚኒስቴሩ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 12/2018(ኢዜአ)፦ በጅማ ከተማ በመንግሥትና በግል ጤና ተቋማት ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት በመስጠት ረገድ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት አበረታች መሆናቸውን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሳህረላ አብዱላሂ ገለፁ።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሳህረላ አብዱላሂ፣ የክልል ጤና ቢሮ ኃላፊዎች፣ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችና አጋር ድርጅቶች በጅማ የሚካሄደውን 27ኛውን የጤና ዘርፍ ዓመታዊ ጉባዔ አስመልክቶ በከተማው የሚገኙ የጤና ተቋማትን ጎብኝተዋል።


 

በጉብኝታቸውም የጅማ ዩኒቨርሲቲ ህክምና ማዕከል፣ የጅማ ከተማ ሞዴል ጤና ጣቢያ እና የኦዳ ሁሌ አጠቃላይ ሆስፒታልን የአገልግሎት አሰጣጥን ተመልክተዋል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሳህረላ አብዱላሂ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት 27ኛው የጤናው ዘርፍ ዓመታዊ ጉባዔ "ዘላቂ ኢንቨስትመንት እና ኢኖቬሽን ለጠንካራ የጤና ሥርዓት" በሚል መሪ ሀሳብ እንደሚካሄድ ተናግረዋል።

በጉብኝቱ እንደሀገር በጤናው ዘርፍ በሽታን የመከላከያና አክሞ የማዳን ስትራቴጂ ማሳካት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን በተጨባጭ መመልከታቸውን ገልጸዋል።

የጅማ ጤና ጣቢያ ለቀዳማይ ልጅነት፣ ለእናቶችና ህፃናት ጤና፣ ለተላላፊና ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች መከላከልና ለማኅበረሰብ ጤና አገልግሎት አሰጣጥ ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን ነው ብለዋል።


 

የግሉ ዘርፍ በጤናው ዘርፍ ላይ ያለው አስተዋጽኦ የሜዲካል ቱሪዝምን ማስፋፋት የሚያስችል የተደራጀና ዘመናዊ የአገልግሎት አሰጣጥ መመልከታቸውንም ነው የገለጹት።

ይህም መንግሥት የግሉ ዘርፍ በስፋት እንዲሳተፍ ያቀረበውን ምቹ ሁኔታ ተጨባጭ ውጤት እያመጣ እንንዳለ የተመለከትንበት ነው ብለዋል።

የጅማ ዩኒቨርሲቲ ህክምና ማዕከል በድንገተኛ ህክምና፣ በጨቅላ ህፃናት ህክምና፣ በካንሰር ህክምና እና የዐይን ባንክን በማቋቋም የጀመረው ሥራ ለሌሎች ምሳሌ እንደሚሆንም አንስተዋል።

የኦክስጅን ማምረቻ በመክፈት ጭምር የጀመረው ተግባር የሚደነቅ መሆኑንና ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ባሻገር በህክምና አገልግሎት አበረታች ተግባራትን እያከናወነ እንዳለም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም