ቀጥታ፡

አርብቶ አደሩን ማህበረሰብ ከእንስሳት ሃብት የበለጠ ተጠቃሚ የማድረግ ተግባራት ይጠናከራሉ

ጂንካ ፤ ጥቅምት 12/2018 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን አርብቶ አደሩን ከእንስሳት ሀብቱ የበለጠ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት እንደሚጠናከሩ የክልሉ መስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

በደቡብ ኦሞ ዞን ጊዜያዊ የእርድ እንስሳት ማቆያ ማዕከላት ከ130 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ሊገነቡ መሆኑም ተመልክቷል።

ለዚህም በበናፀማይ ወረዳና በቱርሚ ከተማ አስተዳደር የተዘጋጀ የሳይት ርክክብ ተደርጓል።


 

በቢሮ የአደጋ ስጋት ቅነሳና አካታች የኢኮኖሚ እሴት ማሻሻያ ፕሮጀክት አስተባባሪ ስዩም መታፈሪያ (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት፤ ደቡብ ኦሞ ዞን አርብቶ አደሩን ከእንስሳት ሀብቱ የበለጠ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ይጠናከራሉ። 

የአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ በሚያረባቸው እንስሳት ብዛት ልክ የበለጠ ተጠቃሚ ሳይሆን መቆየቱን አመልክተው በክልሉም ይህንን ከግምት ባስገባ መልኩ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማጎልበት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።  

ለዚህም በዞኑ በናጸማይና ቱርሚ ከተማ  የኤክስፖርት ስታንዳርድን ያሟሉ የእርድ እንስሳት ጊዜያዊ ማቆያ ማዕከላት ለመገንባት መታቀዱን ገልጸዋል።

የኤክስፖርት ስታንዳርድ ያሟሉ የዕርድ እንስሳት ጊዜያዊ ማቆያ ማዕከላቱ መገንባት አርብቶ አደሩ ከእንስሳት ሀብት የሚገባውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንዲያገኝ ያስችላል ብለዋል።

በክልሉ በአርብቶ አደር አካባቢ ያሉ እንስሳት ሀብትን ጥራት ጠብቆ በሀገሪቱ የሚገኙ ቄራዎችን ፍላጎት ያማከለ የዕርድ እንስሳት አቅርቦት እንዲኖር እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

የፕሮጀክቱ አማካሪ መሀንዲስ ኢንጂነር አዳነ መንገሻ በበኩላቸው ፕሮጀክቶቹ እያንዳንዳቸው በሁለት ሄክታር መሬት ላይ እንደሚያርፉ ገልጸዋል።


 

የፕሮጀክቶቹን ግንባታ በ6 ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ እንደሚሰራና በዛሬው ዕለትም የግንባታ ቦታ ርክክብ መከናወኑን ነው የገለጹት።

የሁለቱን ማዕከላት ግንባታ ለማከናወንም ከ130 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መመደቡን ገልጸው በተያዘው የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።

የጊዜያዊ የዕርድ እንስሳት ማቆያ ማዕከላቱ የእንስሳት ክሊኒክ፣ መኖ ማከማቻ፣ የእንስሳት መመገቢያ እና ማረፊያ ክፍሎች ያሉት መሆኑንም ጠቁመዋል።

በርክክብ ስነ-ስርዓቱ ላይ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ቢሮ፣ የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊዎች፣ የደቡብ ኦሞ ዞን ከፍተኛ አመራር አባላትና የአርብቶ አደሩ ተወካዮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም