በፎረሙ የሚሳተፉ እንግዶች ወደ ክልሉ መምጣት የክልሉን ቱሪዝም ለማነቃቃት ያግዛል - ኢዜአ አማርኛ
በፎረሙ የሚሳተፉ እንግዶች ወደ ክልሉ መምጣት የክልሉን ቱሪዝም ለማነቃቃት ያግዛል

ባህር ዳር፤ጥቅምት 12/2018 (ኢዜአ)፦በጣና ፎረም የሚሳተፉ እንግዶች ወደ ክልሉ መምጣት የክልሉን ቱሪዝም ለማነቃቃት እንደሚያግዝ የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ገለፀ።
የተለያዩ ሃገራት መሪዎችን ጨምሮ ሌሎች እንግዶች የሚሳተፉበት 11ኛው የጣና ፎረም ‘’አፍሪካ በተለዋዋጩ የዓለም ስርዓት’’ በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄድ ይሆናል።
የቢሮ ኃላፊው አቶ መልካሙ ፀጋየ ለኢዜአ እንዳሉት፥ በፎረሙ ለሚሳተፉ እንግዶች የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት በባህር ዳር ከተማ ተደርጓል።
ለዚህም እንግዶቹ የሚያርፉባቸው ሆቴሎች የኢትዮጵያዊያንን ባህል በጠበቀ አግባብ አገልግሎት መስጠት የሚያስችላቸውን ቅድመ ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
አገልግሎት አሰጣጡ እንግዶቹን የሚመጥን እንዲሆንም በባለሙያዎች ድጋፍና ክትትል እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በባህር ዳር በሚካሄደው ፎረም የሃገራት መሪዎች፣ ዲፕሎማቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ ምሁራን እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ይጠበቃሉ።
እነዚሁ እንግዶች በፎረሙ ከመሳተፍ ባሻገር በቆይታቸው የክልሉን ባህል፣እሴትና ወግ የተላበሰ አገልግሎት እንዲያገኙ ይደረጋል ብለዋል።
የፎረሙ ተሳታፊዎች ወደ ክልሉ መምጣትም ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው መነቃቃት የጎላ አስተዋጽኦ እንዳለው አብራርተዋል።
እንግዶቹ በሚሰጣቸው አገልግሎት ልክ ወደ መጡበት አካባቢ ተመልሰው ስለ ክልሉ የቱሪዝም ሁኔታ እንዲያስተዋውቁ በሚያስችል አግባብ ይስተናገዳሉ ብለዋል።
ለዚህም ከኤርፖርት ከሚደረግ አቀባበል ጀምሮ ቆይታቸውን ጨርሰው እስኪመለሱ የመስህብ ስፍራዎችን ጭምር እንዲጎበኙና የሚሸጡ የእደ ጥበብ ውጤቶችን በቀላሉ እንዲያገኙ እንደሚደረግም አመልክተዋል።
እንግዶቹ በሚቆዩባቸው ጊዜያትም ማህበረሰቡ የኢትዮጵያን እንግዳ የመቀበል ባህል አጉልቶ በማሳየት ለፎረሙ መሳካት ሚናውን መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል።
በክልሉ ካሉ የቱሪስት መስህብ ስፍራዎች መካከል የሰሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ፣የላሊበላ ወቅር አብያተ ክርስቲያናት፣የጎንደር አብያተ መንግሥት፣ የአይጠየፍ አዳራሽ፣ የጢስ አባይ ፏፏቴ እና የጣና ገዳማት በዋነኝነት ይጠቀሳሉ።
የፎረሙ የመጀመሪያ ምዕራፍ በባህር ዳር ከተማ ጥቅምት 14 የሚካሄድ ሲሆን ሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ ጥቅምት 15 እና 16/2018 ዓ/ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ መገለፁ ይታወሳል።