በመዲናዋ ከ16 ቢሊየን ብር በላይ የሚያወጡ የተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶችን መስጠት ተችሏል -ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ ከ16 ቢሊየን ብር በላይ የሚያወጡ የተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶችን መስጠት ተችሏል -ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 12/2018(ኢዜአ)፦ በመዲናዋ በ2017 ዓ.ም በበጎ ፈቃድ ስራዎች ከ16 ቢሊየን ብር በላይ የሚያወጡ ሰው ተኮር የልማት ስራዎችን ማከናወን መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
በበጎ ፈቃድ በሚሰጡ ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶች የአቅመ ደካማ ዜጎችን የኑሮ ጫና ማቃለል መቻሉንም ገልጸዋል።
የ2017 ዓ.ም የበጎ ፈቃደኞች የእውቅናና የሽልማት መርኃ ግብር ትላንት ተካሒዷል።
በመርኃ ግብሩ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ መንግስት የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን ገልጸዋል።
በተለይ የአቅመ ደካማ ዜጎችን የኑሮ ሁኔታ የሚያሻሽሉ የልማት ስራዎች በስፋት የተከናወኑ ሲሆን በዚህም የማህበረሰቡ ተሳትፎ የላቀ እንደነበር አስታውቀዋል።
የሀገር እድገትና የዜጎችን የልማት ጥያቄ በመንግስት ጥረት ብቻ መመለስ አዳጋች በመሆኑ በጎ ፈቃደኝነትን በማስረፅ የተከናወኑ የልማት ተግባራት ጉልህ ፋይዳ እንዳላቸው አንስተዋል።
መንግስት የቀረጸው ሰው ተኮር ፖሊሲን በማስፈጸም ረገድ ከተማ አስተዳደሩ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ለዚህም የከተማዋ ነዋሪዎችን በማስተባበር የተከናወኑ ተግባራት ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው ተናግረዋል።
በ2017 በጎ ፈቃድ ስራዎች ከ16 ቢሊየን ብር በላይ የሚያወጡ ሰው ተኮር የልማት ስራዎችን ማከናወን መቻሉንም ተናግረዋል።
በበጎ ፈቃድ በተለያዩ ዘርፎች በተሰማሩ ወጣቶችና ባለሀብቶች በተከናወኑ አገልግሎቶች በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ የተቻለ ሲሆን በተለይ ለአቅመ ደካማ ዜጎች እፎይታን በመስጠት አስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታቸውን ማቃለል ተችሏል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፍቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽነር ይመር ከበደ በበኩላቸው በከተማዋ በሁሉም ዘርፎች ለሚከናወኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የከተማዋ ነዋሪዎች ያበረከቱት አሰተዋጽኦ ጉልህ ፋይዳ እንዳለው አንስተዋል።
በተለይ ወጣቶች፣ አገር በቀል ግብረ ሰናይ ድርጅቶች፣ ተቋማትና ባለሃብቶች በእውቀት፣ በጉልበት፣ በግብአትና በገንዘብ ያደረጉት ድጋፍ የማይተካ ሚና እንዳለውም ጠቁመዋል።
እውቅናው ከተሰጣቸው መካከል አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ በጎ ፍቃደኞች እውቅናው ለቀጣይ ስራ ትልቅ መነቃቃትን የፈጠረ ነው ብለዋል።
የያኔት ስፔሻሊቲ የጥርስ ህክምና መስራች ዶክተር ሃመልማል መንግሰቱ እውቅናው በዘርፉ የተሻለ ስራ ለመስራት የሚያበረታታና ተጨማሪ አቅምን የሚፈጥር ስለመሆኑ ነው የጠቆሙት።
የባቡልኸየር በጎ አደራጎት ድረጀት መስራች ወይዘሮ ሃናን ማህሙድ እንዲሁ እውቅናው ለተጨማሪ ሃላፊነት የአደራ መልእክት ያነገበ ነው ብለዋል።