የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ህብረብሔራዊ አንድነትን ይበልጥ በሚያጠናክር መልኩ ይከበራል -የፌዴሬሽን ምክር ቤት - ኢዜአ አማርኛ
የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ህብረብሔራዊ አንድነትን ይበልጥ በሚያጠናክር መልኩ ይከበራል -የፌዴሬሽን ምክር ቤት

አዳማ፤ ጥቅምት 12/2018 (ኢዜአ)፡-የዘንድሮው 20ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ህብረብሔራዊ አንድነትን ይበልጥ በሚያጠናክር መልኩ እንደሚከበር የፌዴሬሽን ምክር ቤት ገለጸ።
20ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በማስመልከት የትምህርት ተቋማት አመራሮችን በበዓሉ ላይ ግንዛቤ እንዲያስጨብጥ ያለመ የምክክር መድረክ በአዳማ እየተካሄደ ነው።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ በላይ ውድሻ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት ሀገርን ለመገንባትና ለማሳደግ ብዝሃነትን በአግባቡ መያዝና ማስተናገድ ይገባል።
የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ቀን እና ሌሎች አንድነትን የሚያጠናክሩ ሁነቶችን ማስተናገድ ደግሞ ብዝሃነትንና ህብረ ብሔራዊ አንድነትን በአግባቡ ለማስረጽ የጎላ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።
በዓሉን በየዓመቱ ማክበር ብቻ ሳይሆን ዜጎች በህገ መንግስት አስተምህሮ ዙሪያ ተገቢውን ግንዛቤ እንዲይዙ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም አክለዋል።
ባለፉት ዓመታት በፌዴራሊዝምና ህገ መንግስታዊ አስተምህሮ ላይ አተኩረው በተሰሩ ስራዎች በሀገር ልማትና ዕድገት ቀጣይነት፣ ህብረ ብሔራዊነትና የሀገር አንድነትን ከማፅናት አንፃር ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል።
ለ20ኛ ጊዜ ዘንድሮ የሚከበረው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ህብረብሔራዊ አንድነትን ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችሉ ተግባራት በስፋት የሚከናወኑበት መሆኑን ገልጸዋል።
እንዲሁም በፌዴሊዝምና ህገ መንግስት አስተምህሮ ዙሪያ ለዜጎች የተሻለ ግንዛቤ መፍጠር በሚያስችል መልኩ እንደሚከበርም ተናግረዋል።
በዓሉን በታቀደው መሰረት ማክበር እንዲቻል ምሁራን፣ በየደረጃው ያሉ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡም አስገንዝበዋል።
የትምህርት ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸው ተፈራ በበኩላቸው ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጀምሮ በየደረጃው ያሉ የዘርፉ አመራሮችና ሙያተኞች በዓሉን ለማክበር በሚደረገው ሂደት ውስጥ ግንዛቤያቸው እንዲጎለብት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም በትምህርት ተቋማት ያሉ ዜጎች ፌዴራሊዝምና የህገ መንግሥት አስተምህሮ ዙሪያ በቂ ግንዛቤ ጨብጠው ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር እንዲተጉ ያግዛል ብለዋል።
20ኛውን የኢትዮጵያ የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አዘጋጅነት እንደሚከበር መገለጹ ይታወሳል።