ቀጥታ፡

በደሴ ሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማትን ጨምሮ የተለያዩ የመሰረተ ልማት ግንባታ ተጀመረ

ደሴ፤ ጥቅምት 12/2018(ኢዜአ)፦ በደሴ ከተማ አስተዳደር ሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማትን ጨምሮ የተለየዩ የመሰረተ ልማት ግንባታ ዛሬ ተጀምሯል።

በመጀመሪያው ዙር ከ1 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር በላይ የኮሪደር ልማት በማከናወን ለአገልግሎት ክፍት መደረጉ ተመልክቷል።


 

የከተማው አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ በማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓቱ እንደገለጹት፣ የበጀት ዓመቱ የቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ ተጠናቆ ወደ ትግበራ ተገብቷል።

በዚህም የሕብረተሰቡን የልማት ጥያቄ እና የከተማውን የእድገትና አሻጋሪ እቅድ መነሻ በማድረግ በተያዘው በጀት ዓመት ከ20 በላይ ፕሮጀክቶች እንደሚከናወኑ ተናግረዋል።

በዚህም ሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማትን ጨምሮ የበጀት ዓመቱ የተለያዩ የመሰረተ ልማት ግንባታ ሥራዎች ዛሬ በይፋ መጀመሩን አስታውቀዋል።

ከኮሪደር ልማቱ በተጨማሪ የአንድ ኪሎ ሜትር አስፋልት መንገድ፣ የሥራ እድል መፍጠሪያ ሼዶች፣ የጤናና የትምህርት ቤቶች ማስፋፊያ ከፕሮጀክቶቹ መካካል እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው ጊዜ በጥራት እንዲሰሩ ሕብረተሰቡ ሰላሙን በማፅናት የጀመረውን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም መልዕክት አስተላልፈዋል።


 

የደሴ ከተማ አስተዳደር መንገዶች ባለስልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አንዷለም እሸቱ በበኩላቸው፤ ፕሮጀከቶቹ በተያዘላቸው ጊዜ በጥራት እንዲጠናቀቁ የተጠናከረ ክትትልና ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።

ለዚህም አስፈላጊው ግብዓትና ፕሮጀክቶችን መስራት የሚያስችል ዝግጅት ተደርጎ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ዛሬ መጀመሩን አረጋግጠዋል።


 

በፕሮጀክቱ ማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት፤ ከተማ አስተዳደሩ ሕብረተሰቡን በማስተባበር ጭምር ትውልድን ታሳቢ ያደረገ ልማት እየሰራ መሆኑን በማንሳት መደሰታቸውን ገልጸዋል።

ዛሬ የተጀመሩ ልማቶች በስኬት እንዲጠናቀቁ የድርሻቸውን እንደሚወጡም አስታውቀዋል።

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎችም የሕብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም