ጥራቱን የጠበቀ ቡና ለማልማት የሚያስችሉ ተግባራት በስፋት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ጥራቱን የጠበቀ ቡና ለማልማት የሚያስችሉ ተግባራት በስፋት እየተከናወኑ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 12/2018(ኢዜአ)፦ ጥራቱን የጠበቀ ቡና በማልማት ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ተግባራት በስፋት እየተከናወኑ መሆኑን የኦሮሚያና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልሎች ገለጹ።
በግብርናው ዘርፍ ለሀገሪቱ ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ከሚገኙ ምርቶች መካከል ቡና ተጠቃሽ ነው።
ኢትዮጵያም ቡናን ወደ ውጭ በመላክ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እንድታገኝ አቅም እየፈጠረ እንደሚገኝ ይታወቃል።
የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ምክትል ሃላፊ እና የቡናና ፍራፍሬ ልማት ዘርፍ ሃላፊ መሀመድ ሳኒ በክልሉ ቡናን የማልማት ስራ በስፋት እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ቡና ለሀገሪቱ ልማት የሚኖረውን አበርክቶ በአግባቡ ለመጠቀም የቡና ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ያረጁ የቡና ተክሎችን በአዲስ በመተካት፣ የቡና አመራረትን የሚያግዙ ቴክኖሎጂዎችን ጥቅም ላይ በማዋል፣ ተመራጭ የሆኑ የቡና ችግኞችን ለአርሶ አደሮች ማከፋፈልን ጨምሮ በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የቡናና ሻይ ባለስልጣን የቡናና ሻይ ልማት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ካሳሁን ታዬ፤ በክልሉ በቡና ዘርፍ የሚሰሩ ስራዎችን ውጤታማ ለማድረግ ለቡና አመራረት ሂደት ተገቢውን እንክብካቤ እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
እየተከናወኑ ካሉ ተግባራት ውስጥ ምርት የማይሰጡ የቡና ተክሎችን በሌላ የመተካት፣ ምርጥ የሆኑ የቡና ዝርያዎችን ከምርምር ተቋማት ጋር ለአርሶ አደሮች እንዲደርስ የማድረግ ተግባር መጠናከሩን ገልጸዋል።
በተጨማሪም በስፋት የቡና ችግኞች እንዲፈሉ በማድረግ ለተጠቃሚዎች እየቀረበ መሆኑን ተናግረዋል።