በዞኖቹ ከ170 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት ዝግጅት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዞኖቹ ከ170 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት ዝግጅት እየተደረገ ነው
ጊምቢ/ጭሮ ጥቅምት 12/2018(ኢዜአ) ፡-በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ እና ምዕራብ ሀረረጌ ዞኖች ከ170 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የዞኖቹ ግብርና ጽህፈት ቤቶች ገለጹ።
የምዕራብ ወለጋ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት የመስኖ ልማት ባለሙያ አቶ ግርማ ጃለታ እንደተናገሩት በዘንድሮ የበጋ ወራት 95 ሺህ 453 ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት ታቅዷል።
በዞኑ የመስኖ ልማቱ የሚከናወነው መነሲቡ፣ ነጆ፣ ላሎ አሳቢ፣ ሆማ፣ ገንጂ፣ ጊምቢ እና ሓሮ ወረዳዎች ሲሆን በእስካሁኑ እንቅስቃሴ 5 ሺህ 255 ሄክታር መሬት ታርሶ በዘር መሸፈኑን ተናግረዋል፡፡
ምርቱን ለማሳደግ ከ150 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ፣ የውሃ መሳቢያ ፓንፖችን ጨምሮ የግብርና ባለሙያዎች ለአርሶ አደሮች ያልተቋረጠ ክትትልና ድጋፍ እንደሚያድረጉ ጠቅሰዋል፡፡
ልማቱ በኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴና የተለያዩ የግብርና ፓኬጆች በመታገዝ እንደተከናወነ አመልክተው በልማቱም በርካታ አርሶ አርሶ አደሮች ለማሳተፍ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
የመስኖ ስንዴ ልማቱ የዞኑ አርሶ አደሮችን ኑሮ ከማሻሻሉ በላይ ባለፉት ዓመታት በቡና ምርት ብቻ ላይ ተወስኖ የቆየውን አመለካከት በመቀየር ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ እያስቻለ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በአጠቃላይ ከዘንድሮ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 3 ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን አንስተዋል፡፡
በተመሳሳይ በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ከ81 ሺህ 200 ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ለመሸፈን ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን የዞኑ ግብርና ፅህፈት ቤት ገለፀ።
በፅህፈት ቤቱ የስንዴ ልማት አስተባባሪ አቶ ሀቢብ አብዱልከሪም እንደገለፁት በዚህ ዓመት በበጋ መስኖ ስንዴ የሚለማው መሬት ካለፈው ዓመት ከ1 ሺህ 200 ሄክታር በላይ ብልጫ አለው።
እስካሁንም ከአምስት ሺህ ሄክታር በላይ ታርሶ ለዘር መዘጋጀቱን አመልክተዋል።
በዚህ አመት ከሚለማው መሬት ከሶስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ገልፀው ይህም ካለፈው ዓመት ከአንድ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ብልጫ ይኖረዋል ብለዋል።
በዞኑ ባለፈው ዓመት 80 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ መሸፈኑንና ከሁለት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን ገልፀዋል።