ኢትዮጵያ የዓለም የጤና ሽፋን የእውቀት ሽግግር ፕሮግራም ከሚተገበርባቸው ሀገራት መካከል አንዷ ሆና ተመረጠች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የዓለም የጤና ሽፋን የእውቀት ሽግግር ፕሮግራም ከሚተገበርባቸው ሀገራት መካከል አንዷ ሆና ተመረጠች
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 12/2018(ኢዜአ):- ኢትዮጵያ የዓለም የጤና ሽፋን የእውቀት ሽግግር ፕሮግራም (UHC Knowledge Hub) ከሚተገበርባቸው ስምንት ሀገራት መካከል አንዷ ሆና ተመርጣለች።
የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት(አይኤምኤፍ) እና የዓለም ባንክ ዓመታዊ ስብሰባ በዋሺንግተን ዲሲ መካሄዱ ይታወሳል።
የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ከስብሰባው ጎን ለጎን በዓለም አቀፉ የጤና ስራ የመሪዎች ጥምረት ስብሰባ ላይ ተሳትፈዋል።
በመድረኩ የዓለም መሪዎች ጥራቱ የተጠበቀ የጤና አገልግሎት ለሁሉም ተደራሽ የማድረግ ውጥን ያለበትን ደረጃ ተገምግሟል።
የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ የሀገራት የጤና ሪፎርሞች በቀረበበት ወቅት ኢትዮጵያ የማይበገር እና በራስ አቅም የሚመራ የጤና ስርዓት ለመገንባት የያዘችውን ስትራቴጂካዊ ራዕይ አስመለክቶ ገለጻ አድርገዋል።
ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና አገልግሎት ሽፋንን በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደጓን ገልጸዋል።
ለጤናው ዘርፍ ከውጭ የሚደረጉ ድጋፎች መቀነሳቸውን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ መስተጓጎሎች በብሄራዊ ሀብቶች ላይ ጫናውን እያሳደረ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ሚኒስትሩ የኢትዮጵያን የጤና ዘርፍ ለመቀየር የተቀመጡ አራት ስትራቴጂካዊ ምሰሶዎች አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድን ሽፋንን ማስፋት፣ ኢትዮጵያን በጤና ደህንነት በቀጣናው መሪ ማድረግ፣ በቀጣይ ሶስት ዓመታት ውስጥ የጤና ወጪ ውጤታማነትን በ20 በመቶ ማሳደግ እና በጤናው አገልግሎት አቅርቦት የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ማሳደግ የስትራቴጂው የትኩረት መስኮች መሆናቸውን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በመድሃኒት ማምረት ዘርፍ ያላት አቅም እያደገ መምጣቱን ገልጸው በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና አማካኝነት በጤናው መስክ ያሉ የወጪ ንግድ አቅሞችን እንደምትጠቀምም ነው ሚኒስትሩ የገለጹት።
ኢትዮጵያ በፎረሙ የዓለም የጤና ሽፋን የእውቀት ሽግግር እና የአቅም ግንባታ ፕሮግራም ከሚተገበርባቸው ስምንት ሀገራት መካከል አንዷ ሆና ተመርጣለች።
ናይጄሪያ፣ ጋና፣ ኬንያ፣ ግብጽ፣ ካምቦዲያ፣ ፊሊፒንስ እና ኢንዶኔዢያ ሌሎች ፕሮግራሙ የሚተገበርባቸው ሀገራት ናቸው።
ኢትዮጵያ ከልማት አጋሮች ጋር በመሆን የጤና ዘርፍ ውጤቶችን ማሻሻል የሚያስችል ብሄራዊ የቃል ኪዳን ሰነድ(National Health Compact) እያዘጋጀች መሆኑን ጠቁመው ሰነዱ እ.አ.አ ዲሴምበር 2025 በጃፓን ቶኪዮ በሚካሄው የዓለም የጤና ሽፋን ከፍተኛ የምክክር መድረክ ላይ እንደሚቀርብ ገልጸዋል።