ቀጥታ፡

በአማራ ክልል በሩብ ዓመቱ ከሁለት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን በላይ የአንድ ቀን ጫጬቶች ተሰራጭተዋል

ባህር ዳር፤ ጥቅምት 12/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል በሩብ ዓመቱ በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ከሁለት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን በላይ የአንድ ቀን ጫጬቶች መሰራጨታቸውን የክልሉ እንስሳትና አሣ ሃብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮው የዘርፉ ባለሙያ ሙላት ዳኛው ለኢዜአ እንደገለጹት የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብርን ውጤታማ ለማድረግ ለዶሮ እርባታ ተደራሽነት ትኩረት ተሰጥቷል።

ለዚህም በበጀት ዓመቱ ከ13 ሚሊዮን በላይ የአንድ ቀን ጫጩቶችን ለአርቢዎች ለማሰራጨት ታቅዶ በሩብ ዓመቱ ብቻ 2 ሚሊዮን 852ሺህ ጫጩቶችን ማሰራጨት ተችሏል ብለዋል።

‎በዕቅድ የተያዘውን ግብ ለማሳካት የዶሮ ጫጩቶችን የማስፈልፈል፣ የማሳደግና ለአርቢዎች የማሰራጨት ሥራ በቅንጅት እንደሚሰራም አክለዋል።


 

በዶሮ እርባታው ዘርፍ ከተሰማሩ አንቀሳቃሾቸ መካከል የዘምባባ ዶሮ እርባታ ማህበር ሊቀመንበር ወጣት ዮሴፍ ፈቃዱ እንደገለጸው፣ ማህበሩ ሰባት አባላት እንዳሉትና ከመንግስት በተሰጣቸው መስርያ ቦታ 6ሺህ የአንድ ቀን ጫጩቶችን ተረክበው በማሳደግ ላይ ናቸው።

በአሁኑ ወቅት 45 ቀን የሞላቸውን እንቁላል ጣይ ቄብ ዶሮዎችን ለአርቢዎች ለማሰራጨት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ጠቅሷል።

በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የአንድ ቀን ጫጩቶችን አሳድጎ ለአርቢዎች ማሰራጨት ውጤታማ እንደሚያደርግ የገለፀው ደግሞ በባህር ዳር ከተማ በዘርፉ የተሰማራው ወጣት ማስተዋል አያልነህ ነው።

ሁለት ሆነው በመደራጀት በዚህ ሥራ መሰማራታቸውን ጠቁሞ በዓመት እስከ 75ሺህ ጫጩቶችን አሳድገው ለአርቢዎች በማሰራጨት ተጠቃሚነታቸውን እያሳደጉ መሆናቸውን ተናግሯል።

ያለባቸውን የቦታ ችግር የከተማ አስተዳደሩ በቀጣይ ከፈታላቸው ተጨማሪ ጫጩቶችን ተረክበው በማሳደግ ለአርቢዎች በማሰራጨት የተሻለ ተጠቃሚ ለመሆን እንደሚሰሩም ገልጿል።

በክልሉ ባለፈው ዓመት ስድስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን የአንድ ቀን ጫጩቶችን በማስፈልፈል ማሰራጨታቸውን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም