የማሕበረሰብ መድኃኒት ቤቶችን በማስፋፋት አቅርቦትን ለማሻሻል የተጀመረው ስራ ውጤታማ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የማሕበረሰብ መድኃኒት ቤቶችን በማስፋፋት አቅርቦትን ለማሻሻል የተጀመረው ስራ ውጤታማ ነው

ወላይታ ሶዶ ፤ ጥቅምት 12/2018 (ኢዜአ):- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የማሕበረሰብ መድኃኒት ቤቶችን በማስፋፋት የመድኃኒት አቅርቦትን ለማሻሻል የተጀመረው ስራ በውጤማነት መቀጠሉን የክልሉ ጤና ቢሮ ገለጸ።
መድኃኒት በተመጣጣኝ ዋጋ ለማግኘት የማሕበረሰብ መድኃኒት ቤቶች ምቹ ሁኔታ እንደፈጠሩላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ እንዳሻው ሽብሩ ፤ የማሕበረሰብ መድኃኒት ቤቶችን ለማስፋፋት በተደረገ ጥረትም ከ58 በላይ የማሕበረሰብ መድኃኒት ቤቶችን መገንባት መቻሉን ለኢዜአ ገልጸዋል።
ከተገነቡት መድኃኒት ቤቶችም 32ቱ የሰው ኃይል፣ ግብዓትና መድኃኒት ተሟልቶላቸው ስራ ጀምረዋል ብለዋል።
የመድኃኒት ቤቶቹ ወደ ስራ መግባት በሕዝቡ ዘንድ ይነሳ የነበረውን የአቅርቦት ችግር በመፍታት የተሻለ አገልግሎት መስጠት መቻሉን ጠቁመዋል።
አገልግሎቱን በሁሉም መዋቅሮች በማዳረስ የመድኃኒት ስርጭቱን ለማሻሻል በቅንጅት እየተከናወነ ያለው ተግባር በውጤታማነት ተጠናክሮ መቀጠሉን አመልክተው፤ ለዚህም ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።
በከተማ አስተዳደሩ አዲስ የማሕበረሰብ መድኃኒት ቤት ተገንብቶ ስራ መጀመሩን የተናገሩት ደግሞ የወላይታ ሶዶ ከተማ ጤና መምሪያ ምክትል መምሪያ ኃላፊ በረከት ብርሃኑ ናቸው።
ለመድኃኒት ቤቱ ስራ ማስጀመሪያ ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በመመደብ ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህም ከማሕበረሰቡ ይነሳ የነበረውን የመድኃኒት አቅርቦት እጥረት መፍታት መቻሉን ተናግረዋል።
የወላይታ ከተማ ነዋሪዎቹ ወይዘሮ ሮማን አድነው እና አቶ ኢያሱ ጆርጌ በሰጡት አስተያየት፤ የመድኃኒት ቤቶቹ መገንባት የመድኃኒት አቅርቦቱ እንዲሻሻል ከማድረጉም በላይ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።