ቀጥታ፡

በክልሉ የቤት ለቤት የጤና አገልግሎት በሽታን ቀድሞ ከመከላከል ባለፈ የህብረተሰቡን የአኗኗር ዘይቤ እየቀየረ ነው

ሀዋሳ፤ ጥቅምት 12/2018(ኢዜአ)፦ በሲዳማ ክልል የቤት ለቤት የጤና አገልግሎት መጠናከር በሽታን ቀድሞ ከመከላከል ባለፈ የህብረተሰቡን የአኗኗር ዘይቤ እየቀየረ መምጣቱ ተገለጸ።

የክልሉ ጤና ቢሮ በበኩሉ በተያዘው በጀት ዓመት የጤና አደረጃጀቶችን በማጠናከር ሞዴል የጤና ሥርዓት ለመዘርጋት ትኩረት መስጠቱን አስታውቋል፡፡

በሲዳማ ክልል የሚገኙ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች፣ የጤና ልማትና የቤተሰብ ጤና ቡድን መሪዎች ለኢዜአ እንደገለጹት ቤት ለቤት በሚሰጡት የጤና አገልግሎቶች በሽታን ቀድሞ የመከላከል አቅም እየጎለበተና የህብረተሰቡ የአኗኗር ዘይቤ እየተቀየረ መጥቷል።

የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያ ሸርቢቱ ሻዋሌ ከሙያ አጋሮች ጋር በመሆን ከ9ሺህ ለሚበልጡ የቤተሰብ አባላት በጤና ኬላና የቤት ለቤት የጤና አገልግሎት እንደሚሰጡ ገልጸዋል፡፡

በዚህም በተለይ ነፍሰጡር እናቶች የቅድመ ወሊድ ክትትል እንዲያደርጉና በጤና ተቋም እንዲወልዱ ለማድረግ የተሰራው ሥራ የእናቶችና ሕጻናትን ሞት ለመቀነስ አስችሏል ብለዋል።

በተጨማሪም በግልና አካባቢ ንጽህና አጠባበቅ እንዲሁም ተላላፊና ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች መከላከል ላይ የህብረተሰቡን ግንዛቤ የሚያሳድጉ ተከታታይ ውይይቶች በመካሄዳቸው ተጨባጭ ለውጥ መጥቷል ብለዋል፡፡

የወንዶገነት ወረዳ በጎ መልዕክተኛና የጤና ልማት ቡድን መሪ ማሜ ጣቢ በበኩላቸው፣ ከቤት አያያዝ ጀምሮ የመጸዳጃ ቤት እና የአጎበር አጠቃቀም፣ እንዲሁም በሥርዓተ ምግብና በቤተሰብ ምጣኔ ላይ የቤት ለቤት አገልግሎት እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡

በመንደራቸው 30 ሴቶችን በማደራጀት ተከታታይ ውይይት እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰው፣ ቤት ለቤት እየተሰጠ ያለው አገልግሎት የህብረተሰቡን የአኗኗር ዘይቤ እየቀየረና በሽታን ቀድሞ ለመከላከል እያስቻለ ነው ብለዋል፡፡

ማህበረሰቡ በጤና ልማት ሥራው መሪ ተዋንያን እንዲሆን ከጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ጋር በመቀናጀት የቤት ለቤት አገልግሎት እንደሚሰጡ የተናገረችው ደግሞ የወንዶገነት ኬላ ጤና ጣቢያ የቤተሰብ ጤና አገልግሎት ቡድን አስተባባሪ ንግስት ተስፋዬ ናት፡፡

በወጣቶች ማዕከላትና ህብረተሰቡ በሚሰበሰብባቸው አካባቢዎች በጤና ኤክስቴንሽን ፓኮጆች አተገባበር እንዲሁም ተላላፊና ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ላይ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግራለች።

በዚህም የህብረተሰቡን የአኗኗር ዘይቤ ከመቀየር ባለፈ በሽታን ቀድሞ የመከላከል አቅም እያደገ መሆኑን ነው የገለጸችው፡፡

የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ቢሮ ሃላፊ አቶ በላይነህ በቀለ በበኩላቸው እንዳሉት፣ በተያዘው በጀት ዓመት የጤና አደረጃጀቶችን በማጠናከር ሞዴል የጤና ሥርዓት ለመዘርጋት ትኩረት ተሰጥቷል፡፡

በዚህም ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የማህበረሰቡ የጤና ችግር ወደ ማይሆኑበት ደረጃ ለማድረስና ጤናውን በራሱ ማምረት የሚችል ማህበረሰብ ለመፍጠር ግብ ተጥሎ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

የክልሉ ጤና ቢሮ ዓመታዊ ጉባኤ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞና በየደረጃው ያሉ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት መካሄዱ የሚታወስ ነው፡፡

  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም