በአማራ ክልል የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን ማሻሻል የሚያስችሉ የግንባታና ጥገና ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን ማሻሻል የሚያስችሉ የግንባታና ጥገና ተግባራት እየተከናወኑ ነው

ባሕር ዳር፤ ጥቅምት 12/2018(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል በተያዘው የበጀት ዓመት ንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን ለሕብረተሰቡ ይበልጥ ተደራሽ ማድረግ የሚያስችሉ የውሃ ተቋማት ግንባታና ጥገና በመከናወን ላይ እንደሚገኙ የክልሉ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ አስታወቀ።
በተግባሩም ከ577 ሺህ በላይ ሕዝብ የንፁህ መጠጥ ወሃ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተመልክቷል።
የክልሉ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ምክትል ሃላፊ ጥላሁን ሽመልስ፤ በክልሉ ገጠርና ከተሞች የንፁህ መጠጥ ውሃ በበቂ ሁኔታ ተደራሽ የማድረጉ ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል።
በበጀት ዓመቱ ቀደም ሲል የተጀመሩ 35 መካከለኛና ከፍተኛ የውሃ ተቋማት ግንባታ አጠናቆ ለአገልግሎት በማብቃት የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና ተደራሽነት የማሳደግ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
እንዲሁም አንድ ሺህ 465 አነስተኛና መካከለኛ የውሃ ተቋማትን የመገንባት እና በአገልግሎት ብዛት የተጎዱ የውሃ ተቋማትን በመጠገን ለአገልግሎት የማብቃት ስራ እንዲሁ።
በሚገነቡና በሚጠገኑ የውሃ ተቋማት ከ577 ሺህ በላይ የሕብረተሰብ ክፍል የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አብራርተዋል።
የንፁህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የባለድርሻ አካላት ትብብርና እገዛ ወሳኝ እንደሆነ አንስተው፤ ሕብረተሰቡም በገንዘብ፣ በጉልበትና የግንባታ ቁሳቁስ በማቅረብ የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲያጠናከርም አመልክተዋል።
በሌላ በኩል ቢሮው የከተሞችን የፍሳሽና ደረቅ የቆሻሻ አወጋገድ ዘመናዊ ማድረግ የሚያስችሉ ግንባታዎችን በስድስት ከተሞች እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ግንባታዎቹ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በደሴ፣ ጎንደር፣ ደብረ ብርሃን፣ እንጂባራና አረርቲ ከተሞች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው፤ በባሕርዳር ከተማም ግንባታውን ለማስጀመር ዝግጀት እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።
ግንባታዎቹ ሲጠናቀቁ የከተሞችን የቆሻሻ አወጋገድ ዘመናዊ ማድረግ ከማስቻል ባሻገር ቆሻሻን መልሶ ለመጠቀም የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም ከተሞቹን ፅዱ፤ ውብና ለኑሮ ተመራጭ ለማድረግ ታሳቢ ተደርጎ እየተከናወነ እንደሚገኝ አብራርተዋል።