የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የወጪ ንግዱን በከፍተኛ ሁኔታ እያነቃቃው ነው - ኢዜአ አማርኛ
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የወጪ ንግዱን በከፍተኛ ሁኔታ እያነቃቃው ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 12/2018(ኢዜአ)፦ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የወጪ ንግዱን በከፍተኛ ሁኔታ በማነቃቃት ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑን በዘርፉ የተሰማሩ ማህበራት ገለጹ።
ኢትዮጵያ ከሐምሌ 2016 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ትግበራ መግባቷ ይታወቃል።
ገቢራዊ ከተደረገው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ መካከል የብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ማሻሻያ አንዱ ነው።
ማሻሻያው የውጭ ምንዛሪ ስርዓቱን ገበያ መር ማድረጉን ተከትሎ በወጪ ንግድ ላይ የተሰማሩ ባለሃብቶችን ተጠቃሚ እያደረጋችው ይገኛል።
ለአብነትም ቡና፣ አበባ፣ ሰሊጥ፣ የቅባት እህሎች፣ አትክልትና ፍራፍሬ በማምረት ለውጭ ገበያ ለሚያቀርቡ አካላት ማሻሻያው ትልቅ እርምጃ ነው ተብሏል።
የኢትዮጵያ ስጋ አምራቶችና ላኪዎች ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ ከሊፋ ሁሴን ለኢዜአ እንዳሉት፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በተለይ ለስጋ አምራችና ላኪዎች ትልቅ እድል ይዞ መጥቷል።
ማሻሻያው በተለይም ከውጭ ምንዛሪ ተመን ጋር ተያይዞ ማነቆ የነበሩ አሰራሮችን ማቃለል ማስቻሉን ገልጸዋል።
ማሻሻያው ከተደረገ በኋላ በወጪ ንግድ አፈፃፀም ላይ ከፍተኛ ለውጥ መታየቱን ያስታወቁት ሰብሳቢው፤ አሁን ላይ የማህበሩን ገቢ 67 በመቶ ማሳደግ መቻሉን ነው የገለጹት።
በዚህም ባለፉት ሶስት ወራት 5ሺህ ሜትሪክ ቶን የስጋ ምርት በመላክ ከ27 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኝቱን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ አበባና አትክልት አምራቾችና ላኪዎች ማህበር ዋና ዳይሬክተር ቴዎድሮስ ዘውዴ በበኩላቸው፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ዘርፉን በከፍተኛ ሁኔታ ማነቃቃቱን ገልፀዋል።
ከማሻሻያው በኋላ በአበባ ልማትና ምርቱን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ስራ ላይ የተሰማሩ ባለሃብቶች ዘርፉን ለማስፋፋት ዕድል እንደተፈጠረላቸው አስታውቀዋል።
ሪፎርሙ በተለይም ከሆርቲካልቸር ኢንዱስትሪው በቅሬታ ይነሱ የነበሩ አሳሪ ፖሊሲዎችን ለመቀየር ሰፊ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልፀዋል።
ማሻሻያው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ምርቶችን መላክ የሚያስችል ነው ያሉት አቶ ቴዎድሮስ፤ የተወሰዱት እርምጃዎች ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ እያገዙ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ የተሟላ ማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም የወጪ ንግድ አፈፃፀሙን ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረጉን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) ሚኒስቴሩ ከተጠሪ ተቋማት ጋር የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸም በገመገሙበት ወቅት ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱም የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከወጪ ንግድ ከ2 ነጥብ 48 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን መግለጻቸውም ይተዋሳል።