ቀጥታ፡

የአውሮፓ ኃያላኑ ሪያል ማድሪድ እና ጁቬንቱስ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 12/2018(ኢዜአ):- በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዛሬ ዘጠኝ ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።

በሳንቲያጎ በርናባው ስታዲየም ሪያል ማድሪድ ከጁቬንቱስ ምሽት 4 ሰዓት ላይ የሚያደርጉት ጨዋታ የተመልካቾችን ቀልብ ስቧል።

የ15 ጊዜ የሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊ ሪያል ማድሪድ በሊግ ውድድር ፎርማቱ በስድስት ነጥብ ስምንተኛ ደረጃን ይዟል።

የሁለት ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ጁቬንቱስ በሁለት ነጥብ 24 ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ሁለቱ ክለቦች በሻምፒዮንስ ሊጉ ሲገናኙ ለ22ኛ ጊዜ ነው።

ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው 21 የእርስ በእርስ ጨዋታዎች ሪያል ማድሪድ 10 ጨዋታዎችን ሲያሸንፍ ጁቬንቱስ ዘጠኝ ጊዜ ድል ቀንቶታል። ሁለት ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።

በጨዋታዎቹ ሪያል ማድሪድ 25፣ ጁቬንቱስ 26 ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።

ቡድኖቹ ለመጨረሻ ጊዜ በውድድሩ የተገናኙት እ.አ.አ በ2017/18 በሩብ ፍጻሜ ሲሆን ሪያል ማድሪድ በድምር ውጤት 4 ለ 3 በማሸነፍ ግማሽ ፍጻሜውን ተቀላቅሏል።

ሪያል ማድሪድ በላሊጋው በ24 ነጥብ ሊጉን እየመራ የሚገኝ ሲሆን ጁቬንቱስ በሴሪአው በ12 ነጥብ 7ተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

የቡድኖቹ የአውሮፓ መድረክ ፉክክር ከ60 ዓመት በላይ የዘለቀ ነው። የዛሬው ጨዋታም የዚሁ ተቀናቃኝነት ቀጣይ አካል ነው።

የ45 ዓመቱ ስሎቬኒያዊ ስላቫኮ ቪንቺች የሁለቱ ቡድኖች ወሳኝ ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።

ቼልሲ ከአያክስ፣ ኢንትራክት ፍራንክፈርት ከሊቨርፑል፣ ሞናኮ ከቶተንሃም ሆትስፐርስ፣ ባየር ሙኒክ ከክለብ ብሩዥ፣ ስፖርቲንግ ሊዝበን ከማርሴይ እና አትላንታ ከስላቪያ ፕራግ በተመሳሳይ ከምሽቱ አራት ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

አትሌቲኮ ቢልባኦ ከካራባግ እና ጋላታሳራይ ከቦዶ ግሊምት በተመሳሳይ ከምሽቱ 1 ሰዓት ከ45 ላይ ይጫወታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም