ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በሴቶች እግር ኳስ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከታንዛንያ ጋር  ዛሬ ጨዋታዋን ታደርጋለች

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 12/2018(ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ ብሄራዊ ቡድን በ16ኛው የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ የመጨረሻ ዙር ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታውን ከታንዛንያ አቻ ጋር ዛሬ ያከናውናል።

የሁለቱ ሀገራት ጨዋታ ከቀኑ 11 ሰዓት በአዛም ኮምፕሌክስ ስታዲየም ይካሄዳል።

ኢትዮጵያ በመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ ዩጋንዳን በደርሶ መልስ ውጤት በማሸነፍ ለመጨረሻው ዙር አልፋለች።

ተጋጣሚዋ ታንዛንያ ኢኳቶሪያል ጊኒን በድምር ውጤት በማሸነፍ ወደ ወሳኙ ፍልሚያ ተሸጋግራለች።

በአሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድ የሚመራው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ከታንዛንያ ጋር ላለበት ወሳኝ ጨዋታ ለአራት ሳምንታት ገደማ በአዲስ አበባ ዝግጅቱን አድርጓል።

አሰልጣኝ ዮሴፍ ለጨዋታው ዝግጅት ሲያደርግ የነበረውን ስብስብ ወደ 21 በመቀነስ ወደ ታንዛንያ አምርቷል።

ሮማን አምባዬ፣ ቤተልሄም መንተሎ፣ ፀጋ ንጉሤ፣ ቤዛዊት ንጉሤ እና ብዙዓየሁ ታደሰ (በጉዳት) ከስብስቡ የቀነሱ ተጫዋቾች መሆናቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መረጃ ያመለክታል።

ሉሲዎቹ ጥቅምት 10 ቀን 2018 ዓ.ም ዳሬሰላም የገቡ ሲሆን ለጨዋታው የመጨረሻ ልምምዳቸውን በአዛም ኮምፕሌክስ ስታዲየም አድርገዋል።

በባካሪ ሺሜ የሚመራው የታንዛንያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ለጨዋታው በዳሬ ሰላም ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቷል።

ኢትዮጵያ እና ታንዛንያ በውድድና የወዳጅነት ጨዋታዎች ላይ ሲገናኙ የአሁኑ ለስድስተኛ ጊዜ ነው።

ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው አምስት የእርስ በእርስ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ሁለት ጊዜ ስታሸንፍ ታንዛንያ አንድ ጊዜ ድል ቀንቷታል። ሁለት ጊዜ አቻ ተለያይተዋል።

ኢትዮጵያ በጨዋታዎቹ ስድስት ግቦችን ስታስቆጥር ታንዛንያ ሰባት ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፋለች።

ሁለቱ ቡድኖች ኢኳቶሪያል ጊኒ እና ጋቦን እ.አ.አ በ2012 በጣምራ ባዘጋጁት 10ኛው የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ በመጨረሻው ዙር ማጣሪያ ተገናኝተው ኢትዮጵያ በድምር ውጤት በማሸነፍ ለውድድሩ ማለፏ አይዘነጋም።

በፊፋ የሀገራት የእግር ኳስ ደረጃ ኢትዮጵያ 128ኛ፣ ታንዛንያ 131ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

ዩጋንዳዊቷ አይሻ ናሉሊ ጨዋታውን በዋና ዳኝነት ትመራለች።

የሁለቱ ሀገራት የማጣሪያ የመልስ ጨዋታ ጥቅምት 18 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይደረጋል።

ኢትዮጵያ በደርሶ መልስ ውጤት ካሸነፈች በታሪኳ ለአራተኛ ጊዜ በሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ መሳተፏን ታረጋግጣለች።

በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ የሚደረጉ የመጨረሻ ዙር ማጣሪያ ጨዋታዎች ከጥቅምት 12 እስከ 18 ቀን 2018 ዓ.ም ባለው ጊዜ እንደሚካሄዱ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) አስታውቋል።

እ.አ.አ በ2026 በሞሮኮ አስተናጋጅነት በሚካሄደው 16ኛው የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጇን ሀገር ጨምሮ 16 ሀገራት ይሳተፋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም