ቀጥታ፡

የእንስሣትና እጽዋት ብዝኅነት ማኅደር - አልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ

በ266ሺህ 570 ሔክታር ላይ በተንጣለለው አልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ ተፈጥሮ በብዙ መልኮች ትገለጣለች።

በምዕራብ ከሱዳን ዲንደር ብሔራዊ ፓርክ፣ በደቡብ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ በሰሜንና ምሥራቅ ከቋራ ወረዳ ሰባት ቀበሌዎች ጋር እንደሚዋሰን የአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሙላው ሽፈራው ገልጸዋል።

ፓርኩ በተለያዩ ክፍላተ-ዓለማት ብሎም በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ዛፎች፣ እጽዋት፣ የሣር ዓይነቶች እንዲሁም ዝሆን፣ ጎሽ፣ አጋዘን፣ አንበሳ፣ ነብር፣ አዕዋፋት እና ተሳቢ የዱር እንስሣት መኖሪያም ነው ይላሉ።

ለአብነትም፤ ከ32 በላይ ትላልቅ አጥቢ የዱር እንስሣት፣ ከ26 በላይ ትንንሽ አጥቢ የዱር እንስሣት፣ ከ8 በላይ ተሳቢና ተራማጅ የዱር እንስሣት፣ ከ26 በላይ የዓሣ፣ ከ254 በላይ የወፍ፣ ከ130 በላይ የእጽዋት፣ ከ16 በላይ የሌሊት ወፍ ዝርያዎችና ሌሎችም በጥናት በውል ያልተለዩ የተለያዩ እንስሣት መኖሪያ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከእነዚህ መካከል፡- ቀጭኔ፣ ቶራ ፈረስ፣ ጎሽ፣ ወድንቢ፣ የሜዳ ፈል፣ ጨሌባለጋሜ፣ ደፈርሳ፣ አምባራሌ፣ ዝሆን፣ አንበሳ፣ ነብር፣ ድኩላ፣ አጋዘን፣ ጥርኝ፣ ቀፎ ደፊ፣ ከርከሮ፣ ቀይ ጦጣ፣ ፌቆና ሌሎችም መገኛ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሰጎን፣ ቆቅ፣ ጅግራ፣ ንስር፣ ጭልፊት፣ ጭላት፣ ሲላ፣ ገዴ፣ በቀቀን፣ ራዛ፣ ወማይ፣ ንብበል፣ ዋኒ፣ ርግብ፣ ግንደ-ቆርቁር፣ ሸለቆ፣ ዓሣ አውጭ፣ ጉጉት፣ ጥንብ አንሳና ትናንሽ የወፍ ዝርያዎች ወዘተ እንደሚገኙም አንስተዋል።

ሁለት ብርቅየ የዐይጥ ዝርያዎች(white-footed mouse/Stenocephalemys albipes) እና Harrington's Rat (Desmomys harringtoni)፣ ብርቅየና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመጥፋት ከተቃረቡ ዝርያዎች መካከል ባለ ነጭ ጀርባ የአፍሪካ ጥንብ አንሳ (African white backed Vulture (EN) እና ባለነጭ ራስ ጥንብ አንሳ (White headed vulture (VU)፣ Ethiopian Boubou (near Endemic)፣ Bronze-winged Courser (Rare) መገኛ መሆኑንም ይገልጻሉ።

በፓርኩ ከሚገኙ ከ130 በላይ የእጽዋት ዝርያዎች መካከልም፤ ጫምዳ፣ አባሎ፣ ፎረሃ፣ ኩመር፣ ክርክራ፣ ጫሪያ፣ ባምባ፣ የዕጣን፣ ሙጫ፣ ሰሌን፣ አርካ፣ እንኮይ፣ ላሎ የሚባሉ ዛፎችም መገኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የመጥፋት አደጋ ከተጋረጠባቸው 163 የእጽዋት ዝርያዎች መካከል፤ ዲዛ (Adansonia digitata)፣ ዞቢ (Dalbergia melanoxylon)፣ ሰርኪን (Diospyros mespiliformis)፣ ጫሪያ (Pterocarpus lucens)፣ ሽመል (Oxytenanthera abyssinica)፣ ዋልያ መቀር (Boswellia papyrifera) እና ወንበላ (Terminalia laxifora) በፓርኩ ይገኛሉ ብለዋል።

በወቅቱ ብዝኀ-ሕዎትን ለመጠበቅ መከለሉን አውስተው፤ የበረሃማነት መስፋፋትን በመከላከል ለጤናማ ሥርዓተ-ምኅዳር ከፍተኛ ሚና በማበርከቱ በዘርፉ ምሁራን ‘ግሪን ቤልት’ እስከመባል ደርሷል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም