እንደ ሕዳሴው ግድብ ሀገሬውን በአንድነት ያቆመው የባሕር በር - ኢዜአ አማርኛ
እንደ ሕዳሴው ግድብ ሀገሬውን በአንድነት ያቆመው የባሕር በር

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 12/2018 (ኢዜአ)፡- በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የታየው ሕዝባዊነት የባሕር በር ለማግኘት በሚደረገው ሂደትም መስተዋሉን የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ተመራማሪ ያሬድ አያሌው (ዶ/ር) ገለጹ።
የቀደሙት መንግሥታት በስስት ጠብቀው ኢትዮጵያን ለዓለም ያቀረቡበትን የባሕር በር፤ በአንድ ወቅት የነበረ ሕጋዊም ሆነ ሕዝባዊ ድጋፍ የሌለው አካል በምን መነሻና ሞራል አሳልፎ እንደሰጠ ግራ ያጋባል ብለዋል።
የሀገር ፍቅር ካለመኖርና ኢትዮጵያ እንድታድግ ካለመፈለግ የመነጨ ሳይሆን እንዳልቀረ በቦንጋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር እና ተመራማሪ ያሬድ አያሌው(ዶ/ር) ገልጸዋል።
በአሁኑ ትውልድ የባሕር በር ለማግኘት ጥያቄ መነሳቱ ተገቢና ፍትሐዊ መሆኑንም ነው ለኢዜአ ያረጋገጡት።
የባሕር በር ጥያቄው ልክ እንደ ሕዳሴው ግደብ የመላው ኢትዮጵያውን እንጂ የአንድ አካል እንዳልሆነ በሂደቱ ሕዝባዊነት መገንዘባቸውንም ጠቁመዋል።
የባሕር በር ጥያቄ ኢትዮጵያውያንን በመጥቀም ብቻ እንደማይታጠር ገልጸው ኢትዮጵያ የባሕር በር ቢኖራት ጥቅሙ፤ ለአፍሪካ፣ ለመካከለኛው ምሥራቅ፣ ለአውሮፓ እና ለሌሎችም ሀገራት መሆኑን አስገንዝበዋል።
ጥያቄው ተገቢና ፍትሐዊ ቢሆንም ማሳኪያ መንገዶቹ ደግሞ ወሳኝ መሆናቸውን ገልጸው፤ የጎረቤት ችግር የራስም ነውና በሰላማዊ ዲፕሎማሲ ጥረቶችን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ተናግረዋል።
ለዚህም ፖለቲካዊና ሕጋዊ መሠረቶችን ጨምሮ ታሪካዊ ሠነዶችን በመመርኮዝ ከጎረቤት ጀምሮ፣ ለመካከለኛው ምሥራቅ እና ለአውሮፓ፣ ለተጽዕኖ ፈጣሪ ሀገራትና ተቋማት ማስረዳት ይጠበቃል ብለዋል።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ለራሱ ሲል ኢትዮጵያ የባሕር በር እንድታገኝ ማገዝ እንደሚገባው ነው ያስረዱት።