አርሰናል አትሌቲኮ ማድሪድን በሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፏል - ኢዜአ አማርኛ
አርሰናል አትሌቲኮ ማድሪድን በሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፏል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 11/2018 (ኢዜአ)፦ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ተጠባቂ መርሃ ግብር አርሰናል አትሌቲኮ ማድሪድን 4 ለ 0 ረቷል።
ማምሻውን በኤምሬትስ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ቪክቶር ዮኮሬሽ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ጋብርኤል ማጋሌስ እና ጋብርኤል ማርቲኔሊ ቀሪዎቹን ግቦች ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
መድፈኞቹ ከእረፍት መልስ ያሳዩት ድንቅ የማጥቃት እንቅስቃሴ ጨዋታውን እንዲያሸንፉ አድርጓቸዋል።
አርሰናል በሻምፒዮንስ ሊጉ ሶስተኛ ድሉን በማስመዝገብ ነጥቡን ወደ ዘጠኝ ከፍ አድርጓል። አትሌቲኮ ማድሪድ በውድድሩ ሁለተኛ ሽንፈቱን አስተናግዷል።
በሌሎች ጨዋታዎች የወቅቱ የዋንጫ ባለቤት ፒኤስጂ ባየር ሌቨርኩሰንን ከሜዳው ውጪ 7 ለ 2 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፏል።
ዴዚሪ ዱዌ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ኡስማን ዴምቤሌ፣ ክቪቻ ክቫራትሽኬሊያ፣ ቪቲኒያ፣ ዊሊያን ፓቾ እና ኑኖ ሜንዴዝ ቀሪዎቹን ግቦች ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
አሌክስ ጋርሺያ በጨዋታ እና በፍጹም ቅጣት ምት ለሌቨርኩሰን ግቦቹን አስቆጥሯል።
ሮበርት አንድሪች ከሌቨርኩሰን፣ ኢልያ ዛባርኒ ከፒኤስጂ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብተዋል።
ፒኤስጂ በዘጠኝ ነጥብ መሪነቱን አጠናክሯል።
ማንችስተር ሲቲ በአርሊንግ ሃላንድ እና በርናንዶ ሲልቫ ግቦች ቪያሪያልን 2 ለ 0 አሸንፏል።
ኒውካስትል ዩናይትድ ቤኔፊካን 3 ለ 0 ረቷል። ሃርቪ ባርንስ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር አንቶኒ ጎርደን ቀሪዋን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።
ፒኤስቪ ኤይንድሆቨን ናፖሊን 6 ለ 2፣ ኢንተር ሚላን ዩኒየን ሴይንት ዢሎሽን 4 ለ 0 እና ቦሩሲያ ዶርትሙንድ ኮፐንሃገንን 4 ለ 2 አሸንፈዋል።