ኢትዮጵያን የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ የተጀመረውን ጉዞ በጋራ ከዳር ማድረስ ይገባል- አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያን የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ የተጀመረውን ጉዞ በጋራ ከዳር ማድረስ ይገባል- አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 11/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያን የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ የተጀመረውን ጉዞ በጋራ ከዳር ማድረስ እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ተናገሩ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2017 ዓ.ም የበጎ ፈቃደኞች አገልግሎት የእውቅናና የሽልማት መርሃ ግብር በማካሄድ ላይ ይገኛል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በመርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልእክት እንደገለጹት፤ በመላ አገሪቷ በጎ ፈቃደኞችን በማስተባበር በሚከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤት ተመዝግቧል።
በተለይም አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በየዘርፉ በጎ ፈቃደኝነትን ለማስረፅ የሚያደርገው ጥረት በእጅጉ የሚበረታታ ነው ብለዋል።
የዛሬው የእውቅና መርሃ ግብርም በከተማዋ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባር ባህል እየሆነ መምጣቱን የሚያሳይ ነው ብለዋል።
በጎ ፈቃደኝነት የሀገር ፍቅር አንዱ ማሳያ መሆኑን ጠቁመው፤ በዚህ በጎ ተግባር በመሳተፍ አገራቸውንና ህዝባቸውን በቀናነት ላገለገሉ አካላት መንግስት ምስጋና ያቀርባል ብለዋል።
"በጎነት በአንድነት መኖር በአንድነት ማደግ ነው" ያሉት አፈ ጉባኤው፤ ኢትዮጵያን የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ የተጀመረውን ጉዞ በጋራ ከዳር ማድረስ ይገባል ነው ያሉት።
የዛሬው የበጎነት የእውቅና መርሃ ግብር ለሌሎችም ምሳሌ የሚሆንና መነሳሳትን የሚፈጥር መሆኑን አንስተዋል።
በቀጣይም ሁሉም ዜጋ ለበጎ ስራ መተባበር እንዳለበት አመልክተው፤ በዚህም የኢትዮጵያን የማንሰራራት ዘመን እውን ማድረግ ላይ መተባበር እንደሚገባ ተናግረዋል።
#Ethiopian_News_Agency
#ኢዜአ