ቀጥታ፡

በበጎ ፈቃድ በሚሰጡ ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶች የአቅመ ደካማ ዜጎችን የኑሮ ጫና ማቃለል ተችሏል -ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 11/2018(ኢዜአ)፦ በበጎ ፈቃድ በሚሰጡ ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶች የአቅመ ደካማ ዜጎችን የኑሮ ጫና ማቃለል መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ።

የ2017 ዓ.ም የበጎ ፈቃደኞች የእውቅና መርኃ ግብር እየተካሔደ ይገኛል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመርኃ ግብሩ ላይ እንደገለጹት መንግስት የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በርካታ ተግባራትን አከናውናል።

በተለይም የአቅመ ደካማ ዜጎችን የኑሮ ሁኔታ የሚያሻሽሉ የልማት ስራዎች በስፋት መከናወናቸውን ገልፀው በዚህም የማህበረሰቡ የነቃ ተሳትፎ የላቀ እንደነበር ገልጸዋል።

የሀገር እድገትንና የዜጎችን ዘርፈ ብዙ ጥያቄ በመንግስት ጥረት ብቻ መመለስ አዳጋች ነው ያሉት ከንቲባዋ የለውጡ መንግስት በቀረጸው ሰው ተኮር መርኃ ግብር አካታችና አሳታፊ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

በተለይም በጎ ፈቃደኝነትን በማስረፅ የተከናወኑ ተግባራት ጉልህ ፋይዳ እንዳላቸው አንስተዋል።

በከተማዋ በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች፣ በተለያዩ ዘርፎች በተሰማሩ ሙያተኞችና ባለሃብቶች በተከናወኑ አገልግሎቶች በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

አሁን ላይ በጎ ፈቃደኝነት ባህል እየሆነ ከመምጣቱ ባሻገር አንድነት፣ አብሮነትና መደጋገፍ በማህበረሰቡ ዘንድ እንዲሰርፅ እድል መፍጠሩንም ገልጸዋል።

በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በርካታ አቅመ ደካማ ዜጎች ተጠቃሚ እየሆኑ እንደሚገኙም ጠቅሰዋል

በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለተሳተፉ ወጣቶችና ባለሃብቶች ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን እውቅናው በቀጣይ ለሚያደርጉት ተሳትፎ መነቃቃትን ለመፍጠር ያለመ ነው ብለዋል።

#Ethiopian_News_Agency   #ኢዜአ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም