ቀጥታ፡

የወጣቶች ስብዕና መገንቢያ ማዕከላትን የማጠናከር ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል

የወጣቶች ስብዕና መገንቢያ ማዕከላትን የማጠናከር ሥራ ትኩረት መደረጉን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሙና አህመድ ገለጹ።

ከተለያዩ ክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ የወጣት ዘርፍ አመራር አባላት በአዲስ አበባ የሚገኙ የወጣት ስብዕና መገንቢያ ማዕከላትን ጎብኝተዋል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሙና አህመድ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ የወጣት ስብዕና መገንቢያ ማዕከላትን በማጠናከር የታለመላቸውን ዓላማ እንዲወጡ እየተሰራ ይገኛል።

ጉብኝቱም የስብዕና ግንባታን ለማጠናከር እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራትን ወጣቶች እንዲገነዘቡ ለማስቻል ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ የተሰሩ የስብዕና ማዕከላትም የተሻለ ዜጋ ለማፍራት የተከናወኑ ተግባራትን ወደ የክልሎቻቸው በተሞክሮነት እንዲያሰፉ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ወጣትና ስፖርት ምክትል ቢሮ ኃላፊ ክብር-ዓለም ደምሴ በበኩላቸው፤ በመዲናዋ የወጣቶችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ማዕከላት ተገንብተው እየተሰራባቸው ነው።

የክልሎች የወጣት ዘርፍ አደረጃጀት አመራር ጉብኝትም የስብዕና ግንባታ ማዕከላት ላይ በቂ ልምድ እንዲቀስሙ ታልሞ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።

የጉብኝቱ ተሳታፊ የወጣት አመራር አባላት በበኩላቸው፤ በስብዕና መገንቢያ ማዕከላቱ የተሻለ ልምድ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም