በጉራጌ ዞን የተሻሻሉ የዳልጋ ከብት ዝርያዎችን ለአርሶ አደሮች በማቅረብ ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግ ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በጉራጌ ዞን የተሻሻሉ የዳልጋ ከብት ዝርያዎችን ለአርሶ አደሮች በማቅረብ ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግ ተችሏል

ወልቂጤ ፤ ጥቅምት 11/ 2018 (ኢዜአ)፡- በጉራጌ ዞን የተሻሻሉ የዳልጋ ከብት ዝርያዎችን ለአርሶ አደሮች በማቅረብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግ መቻሉን የዞኑ ግብርና መምሪያ ገለጸ።
በዞኑ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ማስጀመሪያ መረሃ ግብር በእንደጋኝ ወረዳ ገነት ቀበሌ ዛሬ ተካሂዷል።
በዚህ ወቅት የመምሪያው ምክትል እና እንስሳት ዘርፍ ኃላፊ አቶ መሐመድ ሙደሲር፤ በዞኑ የዳልጋ ከብት ዝርያንና ጤና አጠባበቅ በማሻሻል ምርታማነታቸውን ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል።
የእንስሳቱ ዝርያ መሻሻልም የወተትና የስጋ ምርትን በማሳደግ የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያደገ መሆኑን ገልጸዋል።
ለአብነት ከነባሩ ዝርያ በቀን በአማካይ ይገኝ የነበረን ሁለት ሊትር ወተት ዝርያቸው ከተሻሻሉ ላሞች ምርቱን በእጥፍ ማሳደግ መቻሉን ጠቅሰዋል ።
ስራውን ለማስፋትም በተያዘው በጀት ዓመት ከ32 ሺህ 490 በላይ እንስሳትን ለማዳቀል ግብ ተይዞ ወደ ተግባር መገባቱን ጠቁመዋል።
የእስሳት ዝርያውን ከማሻሻል ባለፈም ለመኖ ልማት ትኩረት በመሰጠቱ 8 ሺህ 946 ሄክታር ማሳ የእንስሳት መኖ በኩታ ገጠም እየለማ እንደሆነም አክለዋል።
የእንደጋኝ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙሉቀን ገዙ ፤ በእንስሳት ዘርፍ ያለው ፀጋ በመጠቀም የአርሶአደሩን ኑሮ ለማሻሻል በተከናወነው ስራ የተገኘውን ውጤት ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
አርሶ አደሩ ከእንስሳት ቁጥር በመውጣት ኢኮኖሚ ጠቀሜታቸው ከፍ ያሉ የተሻሻሉ ዝርያ ያላቸው የዳልጋ ከብቶች እርባታ ላይ እንዲያተኩር መሰራቱን አንስተዋል።
በሰው ሰራሽ ዘዴ ከተዳቀሉ ላሞቻቸው የተሻለ የወተት ምርት በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የእንደጋኝ ወረዳ አርሶ አደር ሽኩሪያ የኑስ ናቸው።
ዝርያቸው ከተሻሻለ ላሞች በሚያገኙት የወተት ምርት ሽያጭ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው ከማደጉ ባለፈ ከጥጆች ሽያጭ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ሌላው የወረዳው አርሶ አደር በህሩ አብደላ፤ የተሻሻሉ ላሞች በማርባት ቀደምሲል ከሚያገኙት ምርት ከፍ ብሎ በቀን ከ10 ሊትር በላይ ወተት እያገኙ አብራርተዋል።