ቀጥታ፡

አምቦ ዩኒቨርሲቲ የአርሶ አደሩን የግብርና ምርታማነት ይበልጥ ለማሳደግ በምርምር እየደገፈ ነው

አምቦ ፤ጥቅምት 11/2018(ኢዜአ)፡-  አምቦ ዩኒቨርሲቲ  የአርሶ አደሩን  የግብርና ምርታማነት  ማሳደግ   የሚያስችሉ  ዝርያዎችን በምርምር በማወጣት እየደገፈ መሆኑን ገለጸ። 

በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት የተመራ ቡድን በጉደር ማሞ መዘመር ካምፓስ  በምርምር የተከናወኑና በመከናወን ላይ ያሉ የግብርና ሥራዎችን በመስክ  ተመልክቷል።  


 

በወቅቱ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት  ባይሳ ለታ(ዶ/ር) እንዳመለከቱት፤  ተቋሙ ከመማር ማስተማር ተግባሩ ጎን ለጎን የአካባቢውን ማህበረሰብ ህይወት ለማሻሻል የሚያስችሉ ምርምሮችን እያካሄደ ነው።

ሌሎች ድርጅቶችን በማሳተፍ  ጭምር  የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ማሳደግ የሚያስችሉ የሰብል ዝሪያዎችን በምርምር አውጥቶ  ለአርሶ አደሮች ማከፋፈሉን አንስተዋል።

የአካባቢው አርሶ አደር  የቀረቡለትን የተሻሻሉ የሰብል ዝሪያዎች  የተፈጥሮ ማዳበሪያን  በመጠቀም ምርታቸውን ማሳደግ እንዲቻል በተከታታይ የባለሙያዎች ድጋፍ ተደርጎለታል ብለዋል።


 

በዚህም አርሶ አደሩ ውጤታማ መሆኑን ያመለከቱት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት፤ በተጨማሪም የወተት ላሞች እርባታ ፤ የዶሮ እርባታ እና የማር ምርት ከዩኒቨርሲቲው ማሕብረሰብ ባሻገር ለአካባቢው ነዋሪዎች በማቅረብ ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።

የዛሬው የመስክ ጉብኝት ዓላማም ዩኒቨርሲቲው  የምርምርና የማሕበረሰብ  አገልግሎቶችን ለባለድርሻ አካላት ማሳወቅ ብሎም ከሌሎች የምርምር ተቋማት  ጋር የልምድ ልውውጥ ለማድረግ መሆኑን  የገለጹት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የጉደር ማሞ መዘመር ካምፖስ ዳይሬክተር ንጉሴ በቀለ ( ዶ/ር ) ናቸው፡፡


 

በካምፓሱ የሰብል ምርምር ፤ የወተት ላሞች እና የዶሮ እርባታዎችን  አርሶ አደሩና ሌላውም ማህበረሰብ  በማሳተፍ ጭምር በመደገፍ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ሌላው የመስክ ጉብኝቱ ላይ የተገኙት የግብርና ተማራማሪ ተስፋዬ ሽፈራው(ዶ/ር) እንዳሉት፤ ከአምቦ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመቀናጀት በሚያደርጉት የምርምር ስራ የተሻለ ውጤት እየተገኘ ነው።

በዚህም ለአካባቢው ነዋሪዎችም  በምርምር የተገኙ የተለያዩ የሰብል ዝሪያዎችን፣  የተሻሻሉ የወተት ላሞችንና ዶሮዎችን  እያቀረብን ነው ብለዋል።


 

የቶኬ ኩታዬ ወራዳ ነዋሪ ወይዘሮ ሙሉ እመቤት ኢዶሳ በሰጡት አስተያየት፤ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የጉደር ማሞ መዘመር ካምፓስ  የተለያየ  ድጋፍ እያደረገላቸው መሆኑን ገልጸዋል። 

ከካምፓሱ ከሶስት ዓመት በፊት  የወተት ላም  እንደተሰጣቸው ያስታወሱት ወይዘሮ ሙሉ እመቤት ፤ ላሟ ሶስት ጥጃዎች በመውለዷ ተጠቃሚ እየሆንኩ ነው ብለዋል።


 

በተጨማሪም  የተሻሻሉ የሰብል ዝሪያዎችን እንደሰጧቸው ጠቅሰው፤  ተቋሙ ለሌሎች የአካባቢው  ነዋሪዎች  ተመሳሳይ ድጋፍ  ማድረጉን  ተናግረዋል። 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም