በባቡር መሰረተ ልማት ግንባታ ለሚሰማሩ የግል ባለሃብቶች አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል - ሚኒስቴሩ - ኢዜአ አማርኛ
በባቡር መሰረተ ልማት ግንባታ ለሚሰማሩ የግል ባለሃብቶች አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል - ሚኒስቴሩ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 11/2018(ኢዜአ)፦ በባቡር መሰረተ ልማት ግንባታ ለሚሰማሩ የግል ባለሃብቶች አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ዴንጌ ቦሩ ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ባለድርሻ አካላት፣ የፋይናንስ ተቋማት፣ አምባሳደሮች፣ ባለሃብቶችና የልማት አጋሮች በተገኙበት ብሔራዊ የባቡር ቢዝነስና ኢንቨስትመንት መድረክ አካሒዷል፡፡
የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ዴንጌ ቦሩ በዚሁ ወቅት፤ የባቡር ትራንስፖርት አህጉራዊ የሎጅስቲክስ እና የንግድ እንቅስቃሴን ለማሳለጥ ጉልህ ሚና ያበርክታል ብለዋል፡፡
በተለይም የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር ለንግድና ሎጀስቲክስ መሳለጥ የጀርባ አጥንት ሆኖ እያገለገለ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
አሁን ላይ በቂ የባቡር መሰረተ ልማት ባለመኖሩ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡና ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶች በአብዛኛው የሚጓጓዙት በመኪና መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ይህም ከፍተኛ የጊዜ እና የገንዘብ ብክነት ከማስከተሉ ባሻገር የኢትዮጵያ ምርቶች በዓለም አቀፍ ገበያ በወቅቱ እንዳይደርሱና ተወዳዳሪነታቸው እንዲቀንስ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል፡፡
መንግስት በአሁኑ ወቅት ለባቡር ትራንስፖርት ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ዘርፉ ለግል ባለሃብቱም እንዲመች ሆኖ መደራጀቱንና ለሚሰማሩ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ህሊና በላቸው በበኩላቸው፤ ኮርፖሬሽኑ የባቡር መሰረተ ልማት፣ የሎጂስቲክስ ማዕከልና ሌሎችም የቢዝነስ ፕሮጀክቶችን ይፋ ማድረጉን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በራሷ አቅም የባቡር መሠረት ልማቶችን ለማከናወን የተለያዩ ጥረቶች እያደረገች እንደምትገኝ በመጥቀስ።
በሶፍዑመር ዋሻ አካባቢ የተሰራውን የሁለት ኪሎ ሜትር የባቡር መስመር ዝርጋታ በማሳያነት አንስተዋል።
በቀጣይ የባቡር መሰረተ ልማቶችን እና ዛሬ ይፋ የተደረጉ ፕሮጀክቶችን በላቀ መልኩ ለመገንባትና ለማስፋፋት የግል ባለሃብቱ ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
በአፍሪካ ህብረት የመሰረተ ልማትና ኢነርጂ ዘርፍ ኮሚሽነር ለሬቶ ማታቦጅ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የባቡር መሰረተ ልማት ግንባታን ለማስፋፋት እየወሰደችው ያለው እርምጃ አፍሪካን የማስተሳሰር አካል ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ቀጠናውን በኢኮኖሚና በመሰረተ ልማት ለማስተሳሰር የጀመረችውን ጥረት ለማገዝ ህብረቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ በማረጋገጥ፡፡
የድሬዳዋ መልካ ጀብዱ የባቡር መንገድ፣ የሞጆ የተቀናጀ አነስተኛ የወደብ ከተማ ግንባታ የአንዶዴ የሎጀስቲክስ ወደብ ልማትና የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ሁለ ገብ ህንጻ በዛሬው እለት ይፋ ከተደረጉ የባቡር መሰረተ-ልማቶች መካከል ይገኙበታል፡፡