ቀጥታ፡

ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን የጠበቀ የቡና ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶታል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 11/2018(ኢዜአ)፦ ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን የጠበቀ የቡና ምርትና ምርታማነት ማሳደግና የቡና መረጃዎችን ዘመኑን በዋጀ አግባብ ለማደራጀት የሚያስችሉ ተግባራት በትኩረት እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።

ባለስልጣኑ የቡና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያግዙ 100 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው የመረጃ መሰብሰቢያ ዘመናዊ ስልኮችንና ለቡና ጉንደላ የሚያገለግሉ ግብአቶችን ዛሬ ለክልሎች አስረክቧል።

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) ባለፈው ዓመት ለውጭ ገበያ ከቀረበው ቡና 40 በመቶ የሚሆነው ለአውሮፓ ሀገራት መላኩን አስታውሰዋል፡፡

ይህንኑ ለማስቀጠል በርካታ የቤት ስራ ይጠብቀናል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ የአውሮፓ ህብረት ወደ አህጉሩ የሚገቡ የቡና ምርቶች ከደን ምንጣሮ ነጻ ሊሆኑ ይገባል የሚል አሰራር ማስቀመጡን ተናግረዋል።

በዚህም ወደ አውሮፓ ሀገራት ቡና ለመላክ የተቀመጡትን መስፈርቶች በተመለከተ ለባለድርሻ አካላት ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ባለስልጣኑ በየክልሎች ለሚገኙ አስፈጻሚዎች ስልጠና በመስጠትና ለዘርፉ ተዋናዮች የቡናን ምርትና ምርታማነት የሚያሳድጉ ግብአቶች ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በቡና ምርት ላይ የተሰማሩ ዜጎችን የተመለከቱ መረጃዎችን በአግባቡ ለማደራጀት የሚያስችል ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

በዚህም ባለስልጣኑ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር መረጃ ለመሰብሰብ የሚረዳ ዘመናዊ የስልክ ቀፎ እና ለቡና ጉንደላ የሚያገለግሉ ግብዓቶችን ለክልሎች ማስረከቡን ጠቅሰዋል።

ይህም ኢትዮጵያ ቡናን ከደን ምንጣሮ ነጻ በሆነ ቦታ ላይ እያለማች እንደምትገኝ የሚገልጽ መረጃ በቀላሉ ለማቅረብ ያስችላል ብለዋል።


 

የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ታጋይ ኑሩ በበኩላቸው መረጃ የማደራጀት ስራ የቡና አመራረት ከደን ምንጣሮ በጸዳ መልኩ ለመከናወኑ ማረጋገጫ ከማቅረብ ባለፈ ከቡና ጋር የተያያዙ መረጃዎችን የማደራጀት አቅም ይፈጥራል ብለዋል።

መረጃዎቹ በቡና ምርታማነት ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን በመለየት ለችግሮች አፋጣኝ መፍትሄ ለመስጠት እንደሚያስችሉ ጠቅሰዋል።


 

የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ምክትል ሃላፊ እና የቡናና ፍራፍሬ ልማት ዘርፍ ሃላፊ መሀመድ ሳኒ አሚን በበኩላቸው የተደረገላቸው ድጋፍ መረጃን መሰረት በማድረግ የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ አቅም እንደሚፈጥር ተናግረዋል።


 

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የቡናና ሻይ ልማት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ካሳሁን ታዬ በበኩላቸው የቡና ምርታማነትን ለማሳደግ የተደረገውን ድጋፍ በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም