ለአህጉሪቱ የምግብ ዋስትና ችግሮች ዘላቂ ምላሽ ለመስጠት አባል ሀገራት አፋጣኝ የመፍትሔ እርምጃ መውሰድ ይኖርባቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
ለአህጉሪቱ የምግብ ዋስትና ችግሮች ዘላቂ ምላሽ ለመስጠት አባል ሀገራት አፋጣኝ የመፍትሔ እርምጃ መውሰድ ይኖርባቸዋል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 11/2018(ኢዜአ)፦ ለአህጉሪቱ የምግብ ዋስትና ችግሮች ዘላቂ ምላሽ ለመስጠት አባል ሀገራት በትብብር ላይ የተመሠረተ አፋጣኝ የመፍትሔ እርምጃ መውሰድ እንደሚኖርባቸው በአፍሪካ ሕብረት የግብርና፣ የገጠር ልማት፣ የብሉ ኢኮኖሚና ዘላቂ አካባቢ ኮሚሽነር ሞሰስ ቬላካቲ አስገነዘቡ።
የአፍሪካ ሕብረት የገጠር ግብርና ልማት፣ የውሃና አካባቢ ልዩ የቴክኒክ ኮሚቴ 6ኛ መደበኛ ስብሰባውን ’’በአፍሪካ አስተማማኝና ዘላቂ የምግብ ሥርዓት መገንባት’’ በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ ማካሄድ ጀምሯል።
በአፍሪካ ሕብረት የግብርና፣ የገጠር ልማት፣ የብሉ ኢኮኖሚና ዘላቂ አካባቢ ኮሚሽነር ሞሰስ ቬላካቲ ቪላካቲ÷ የመሬትና የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀምን በማሻሻል የግብርና ምርታማነትን ማሳደግ ያስፈልጋል ብለዋል።
አፍሪካ በየዓመቱ ከ50 እስከ 100 ቢሊዮን ዶላር የምግብ ምርቶችን ከውጭ ታስገባለች ያሉት ኮሚሽነሩ÷ ይህም የግብርና ምርታማነትን በማዘመን ማስቀረት የሚቻል መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።
የመሬት አያያዝ ችግሮችና የምርታማነት ጉድለቶች የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ፈተና መደቀናቸውን አስገንዝበዋል።
በመሆኑም የአህጉሪቱ አባል ሀገራት የምግብ ሥርዓትን ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት ማነቆዎችን በአፋጣኝና በዘላቂነት በመፍታት የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ አንደሚኖርባቸው አስረድተዋል።
በአፍሪካ ህብረት የዓለም የምግብ ፕሮግራም ተወካይ ሐመድ ኑሩ÷ አፍሪካ የግብርና ፈጠራ አቅሞችን በማጎልበት የወጣቶችና ሴቶች ተጠቃሚነት የሚያሻሽል ሀገር በቀል የምግብና የግብርና ስርዓትን መተግበር አለባት ብለዋል።
የግብርና ምርምር ማዕከላትና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተከናወኑ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ወደ ተግባር በመለወጥ የግብርና ምርታማነትን ማሻሻል እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
በአፍሪካ ሕብረት የአውሮፓ ሕብረት ልዑክ ማቲያስ ሬዑሲንግ÷ የአፍሪካን መፃኢ እጣ ፋንታ የተሻለ ለማድረግ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በቀጣይም የአፍሪካውያንን ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚደረጉ ጥረቶች የሚያደርጉት ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
እስከ ጥቅምት 14/2018 ዓ.ም ለአራት ተከታታይ ቀናት በሚቆየው ስብሰባ በ5ኛው ስብሰባ እና በማላቦ አጀንዳ የውሳኔ አፈፃፀም ላይ ምክክር ይደረጋል።
በጉባኤው የማጠናቀቂያ ቀንም የሕብረቱ አባል ሀገራት ሚኒስትሮችና የልማት አጋሮች በተገኙበት ከ2026 እስከ 2035 በአህጉሪቱ የሚተገበረው የካምፓላ አጀንዳ ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።