ቀጥታ፡

በተፈጥሮ ጋዝ የሚሰሩ 150 ተሽከርካሪዎች ከቻይና ወደ ሀገር ውስጥ ሊገቡ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 11/2018(ኢዜአ)፦ በተፈጥሮ ጋዝ የሚሰሩ 150 ተሽከርካሪዎች ከቻይና ወደ ሀገር ውስጥ ሊገቡ መሆኑ ተገለጸ።

በፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ከቻይና ማስመጣት የሚያስችል ስምምነት ተፈርሟል።

ስምምነቱ የተፈረመው በኢትዮ-ቻይና ንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም ላይ ሲሆን፤ ተሽከርካሪዎቹ በተያዘው ዓመት ስራ ይጀምራሉ ተብሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሶማሌ ክልል ካሉብ በዓመት 111 ሚሊዮን ሊትር ማምረት የሚችለውን የኦጋዴን ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ዙር በይፋ በመመረቅ የጎዴ ነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ማሰቀመጣቸው ይታወሳል።

ይህን ተከትሎ የገንዘብ ሚኒስቴር በተፈጥሮ ጋዝ የሚሰሩ ማናቸውም ዓይነት የደረቅና የፈሳሽ ጭነት እና የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ከጉምሩክ ቀረጥ ነፃ ሆነው ወደ ሀገር እንዲገቡ መፈቀዱን መግለጹ ይታወቃል።

ይህንኑ መሰረት በማድረግ ቢአኤካ ጄኔራል ቢዝነስ 150 በተፈጥሮ ጋዝ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ከቻይና ሻክማን ኩባንያ ማምጣት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራርሟል።


 

ቢአኤካ ግሩፕ በተፈጥሮ ጋዝና በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ከማስመጣት ባለፈ በሀገር ውስጥ መገጣጠም የሚያስችል ፋብሪካ እየገነባ መሆኑን የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሚካኤል ካሳ ገልጸዋል።

በተፈጥሮ ጋዝና በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች የውጭ ምንዛሬን በማዳን ለሀገር ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት ከፍተኛ ሚና እንዳላቸውም ተናግረዋል።


 

የሻክማን ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሚስተር ጂ በበኩላቸው፤ በተፈጥሮ ጋዝ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ወደ ስራ መግባታቸው የነዳጅ ወጪንና የአካበቢ ብክለትን ለመቀነስ ከፍተኛ ሚና አላቸው ብለዋል።

ተሽከርካሪዎቹ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተገጠመላቸው መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገቡ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም