በደሴ ከተማ በማህበር ተደራጅተው በተለያዩ የስራ መስኮች ላይ የተሰማሩ ሴቶች ውጤታማ መሆን ችለዋል - ኢዜአ አማርኛ
በደሴ ከተማ በማህበር ተደራጅተው በተለያዩ የስራ መስኮች ላይ የተሰማሩ ሴቶች ውጤታማ መሆን ችለዋል

ደሴ፤ ጥቅምት 11/2018(ኢዜአ)፡ - በደሴ ከተማ በማህበር ተደራጅተው በተለያዩ የስራ መስኮች የተሰማሩ ሴቶች ውጤታማ መሆናቸውን ተናገሩ።
የክልሉ፣ የዞንና የደሴ ከተማ አስተዳደር ሴት አመራሮችና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በደሴ ከተማ በልማት ሕብረት በተደራጁ ሴቶች የተከናወኑ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።
የሴቶቹ የስራ ዘርፎች የባልትና ውጤቶችና የሌማት ትሩፋት መርሃ ገብርን ጨምሮ ሌሎችም ይገኙበታል።
በሴቶች የልማት ሕብረት ሶስት ሆነው በመደራጀት በባልትና ስራ ላይ ከተሰማሩት መካከል ወይዘሮ ዘሪቱ ጌታቸው፤ የተለያዩ የባልትና ውጤቶችን በማዘጋጀት ለገበያ በማቅረብ ትርፋማ መሆናቸውንና ለ30 ሴቶችም የሥራ እድል መፍጠር መቻላቸውን ተናግረዋል።
ሌላዋ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ አሊማ አስፋው የከተማ አስተዳደሩ ባመቻቸላቸው መሬት የተለያዩ አትክልቶችን በማልማት ከቤት ፍጆታ አልፈው ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በወተት ላም እርባታ ላይ የተሰማሩት ወይዘሮ ወርቄ ከልካይም፤ በቀን ከ400 ሊትር በላይ ወተት ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በጥቂት ላሞች የጀመሩት ስራ አሁን ላይ ቁጥራቸው ጨምሮ 43 መድረሱን ጠቅሰው ፤ ስራውን አጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን ገልጸዋል።
የደሴ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ምሳዬ ከድር፤ በሴቶች ልማት ሕብረት ከ71 ሺህ በላይ ሴቶች ተደራጅተው ወደ ስራ መግባታቸውን ገልጸው፤ በየተሰማሩባቸው ዘርፎችም ውጤታማ ሆነዋል ብለዋል።
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ዝና ጌታቸው በበኩላቸው፤ ሴቶችን በማደራጀት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን በማረጋገጥ ረገድ የተጀመሩ ጥረቶች ውጤት እያታየባቸው መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይም ከኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትም ባለፈ በፖለቲካና ማህበራዊ ዘርፎችም ጠንካራ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ይሰራል ሲሉ አረጋግጠዋል።