በክልሉ በስርዓተ ፆታ አካታችነት በማጠናከር የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ተግባር እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በስርዓተ ፆታ አካታችነት በማጠናከር የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ተግባር እየተከናወነ ነው

አዳማ፤ ጥቅምት 11/2018 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ የስርዓተ ፆታ አካታችነት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ገለፀ።
ቢሮው በክልሉ በስርዓተ ፆታ እኩልነት አተገባበርና በታዩ ውስንነቶች ላይ ከኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርስቲና ከክልሉ የስራ ዕድል ፈጠራ ቢሮ ጋር በመተባበር ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የምክክር መድረክ በአዳማ አካሄዷል።
የኦሮሚያ ክልል ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ መብራት ባጫ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት በክልሉ የስርዓተ ፆታ እኩልነትን ከማረጋገጥ አንጻር የሚታዩ ውስንነቶችን ለመፍታት ትኩረት ተደርጓል።
በተለይ በክልሉ የመንግሥት መዋቅሮች የስርዓተ ፆታ እኩልነት እንዲረጋገጥ እንዲሁም የህፃናትን መብትና ደህንነት የማስጠበቅ ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
በዚህም የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ማነቆ የሆኑ ችግሮች እየተፈቱ መሆኑንም ተናግረዋል።
ሴቶች ከኢኮኖሚ ጥገኝነት እንዲላቀቁና ራሳቸውን እንዲችሉ በግብርና፣ በአገልግሎትና በተለያዩ የስራ መስኮች ተሳትፏቸው እንዲጎለብት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው በበጎ ፈቃድ አገልግሎትም ግንባር ቀደም ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተደረገ ነው ብለዋል።
የዛሬው መድረክም በክልሉ መንግሰት መዋቅር ውስጥ በስርዓተ ፆታ እኩልነትና ተግባራዊነት ላይ የተገኙ ውጤታማ ተሞክሮዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠልና የተለዩ ክፍተቶችን ለመሙላት በጋራ ዕቅድ የተደገፈ የተቀናጀ ርብርብ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል።
በጨፌ ኦሮሚያ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ መስታወት ፈይሳ፣ የምክር ቤት አባላቱ በዕቅድና በመስክ ምልክታ የሴቶችን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አንፃር አበረታች ስራዎች እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይ ከዕቅድ ጀምሮ ከወረዳ እስከ ክልሉ የመንግስት መዋቅር ድረስ በየደረጃው ባለው ተቋማት የስርዓተ ፆታ እኩልነት ትግበራ ላይ ክትትል እየተደረገ ነው ብለዋል።
''የስርዓተ ፆታን ተግባራዊነት ከማረጋገጥ አንፃር ከተቋም ተቋም ልዩነት ቢኖርም መሻሻል አለ'' ያሉት ሰብሳቢዋ በተለይ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ከማረጋገጥና ሴቶች ወደ ውሳኔ ሰጪነት እንዲመጡ ከማድረግ አንፃር አበረታች ውጤት እየታየ መሆኑን ገልጸዋል።
የሴቶችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አኳያ በስራ ዕድል ፈጠራና ሴቶች በገቢ ራሳቸውን እንዲችሉ በተቀናጀ መልኩ መሰራት እንዳለበትም አመለክተዋል።
የኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርስቲ ተመራማሪ አቶ ሀብታሙ ደሳለኝ በበኩላቸው የስርዓተ ፆታ እኩልነትን ለማረጋገጥ የተቀናጀ እና በዕቅድ የሚመራ ስራ ማከናወን ያስፈልጋል ብለዋል።
በስርዓተ ፆታ ተግባራት ዙሪያ ያለው ግንዛቤ በሁሉም መልኩ ማደጉ፣ የሴቶች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትና ውሳኔ ሰጪነት ሚና እያደገ መምጣቱ አበረታች ጥረት መሆኑን አስረድተዋል።
በዩኒቨርስቲው አማካኝነት በስርዓተ ፆታ እኩልነትና ተግባራዊነት ላይ አተኩሮ ጥናት መካሄዱን ገልጸው በጥናቱ መሰረትም መሻሻሎች ቢኖሩም በርካታ ስራዎች ይቀራሉ ብለዋል።