ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ከአሜሪካ የግምጃ ቤት እና ስቴት ዲፓርትመንት የስራ ሀላፊዎች ጋር የኢኮኖሚ ትብብርን ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ መከሩ - ኢዜአ አማርኛ
ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ከአሜሪካ የግምጃ ቤት እና ስቴት ዲፓርትመንት የስራ ሀላፊዎች ጋር የኢኮኖሚ ትብብርን ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ መከሩ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 11/2018(ኢዜአ)፦ በገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ የተመራው የኢትዮጵያ ልዑክ ከአሜሪካ የግምጃ ቤት እና ስቴት ዲፓርትመንት የስራ ሀላፊዎች ጋር የኢኮኖሚ ትብብርን ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።
ውይይቱ የተካሄደው የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) እና የዓለም ባንክ ዓመታዊ ስብሰባ ጎን ለጎን ነው።
በውይይቱም አቶ አህመድ ሽዴ የኢትዮጵያን ወቅታዊ የልማትና ዕድገት ሁኔታ እንዲሁም የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም ትግበራ ሂደትን የተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም መንግስት ግልጸኝነትን ለማስፈን፣ የመንግስት አስተዳደርን ለማጠናከርና የቢዝነስና ኢንቨስትመንት ምህዳሩን የበለጠ ለማስፋት ቁርጠኛ መሆኑን በአጽንኦት አንስተዋል።
ውይይቱ በሁለቱ ሀገራት የጋራ ጥቅሞች በሆኑ ማለትም አሜሪካ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሪፎርም የምታደርገውን ድጋፍ በተለይ በባለብዙ ወገን ባንኮችና በዓለም ገንዘብ ድርጅት በኩል እንዲሁም በንግድና ኢንቨስትመንት ያላቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልባቸው ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እንደነበር ተመላክቷል።
የአሜሪካ የስራ ሀላፊዎች በበኩላቸው አሜሪካ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሪፎርም ውጤታማነት የቴክኒክ ድጋፍን ጨምሮ በግሉ ዘርፍ በመሳተፍ እና ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ጋር በመተባበር የምታደርገውን ድጋፍ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።
ሁለቱ ወገኖች ቀዳሚ በሆኑና ቀጣይነት ያለው ዕድገት ማስመዝገብ በሚያስችሉ የጋራ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮቻቸው ላይ የሚያደርጉትን ውይይት አጠናክሮ ለማስቀጠል ተስማምተዋል።