ቀጥታ፡

የሕዳሴ ግድብ ዓለም አቀፍ ጫናዎችን ተቋቁሞ መጨረስ እንደሚቻል አሳይቷል፤ የቀድሞ ትርክትን ቀይሯል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 11/2018(ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ ጫናዎችን ተቋቁማ መፈጸም እንደምትችል ያሳየ፤ ዓባይ ግንድ ይዞ ይዞራል የሚለውን ትርክት የቀየረ ነው ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች ገለጹ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አማካሪ ኮሚቴ እና አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት እንዲሁም የጽሕፈት ቤት የሥራ ኃላፊዎች ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጎብኝተዋል፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አማረች በካሎ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ከፍ ብላ እንድትታይ አድርጓል፡፡

ለዘመናት ሲነገር የቆየው "ዓባይ ግንድ ይዞ ይዞራል" የሚለው ትርክት በአዲስ አስተሳሰብ በመቀየር የኢትዮጵያውያንን መቻል ገልጧል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ሀገራዊ ብልጽግና የሚያረጋግጡ ትልልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን የትኛውም ዓለም አቀፍ ጫና ሳይበግራት መፈጸም እንደምትችል ማረጋገጫ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ሀብታችንን በፍትሐዊነት በመጠቀም ለቀጣናው ልማትና ትስስር በጋራ እንድምንሰራ ዳግም ያረጋገጥንበት ፕሮጀክታችንም ነው ብለዋል፡፡


 

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደሳለኝ ወዳጆ፤ የሕዳሴ ግድብ ህዝቡን በፈቃደኝነት ማነሳሳት ትልቅ የፋይናንስ አቅም መሆኑን አረጋግጧል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከድህነት ለመላቀቅ በራሷ የበጀት አቅም ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ማድረግ እንድምትችል ማስተማሪያ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በውጭ ብድር ቢጀመር ኖሮ ለዘመናት እንደቆመ ይቀራል እንጂ አይጠናቀቅም ነበር ብለዋል፡፡

በግንባታ ወቅት ሲደርሱ የቆዩት ዓለም አቀፍ ጫናዎች ትልቅ ማሳያዎች ናቸው ያሉት ሰብሳቢው፤ የሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ አቅሟን ያሳየችበት ለነገ ልምድ የወሰደችበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡


 

በምክር ቤቱ የውሃ፣ መስኖና ቆላማ አካባቢዎች እና አካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ፈቲያ አህመድ በበኩላቸው፤ የሕዳሴ ግድብ የመላ ኢትዮጵያውያን የላብ የደምና የእንባ ጠብታ ድምር ውጤት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሕዳሴ የኢትዮጵያውያን አንድነትና ትብብር ማጠናከሪያ፣ የአይበገሬነት ማሳያ እና የቁርጠኝነታቸው ማረጋገጫ ነው ብለዋል፡፡

በሁሉም የዓለም ማዕዘን ያሉ ኢትዮጵያውያን ከሊቅ እስከ ደቂቅ፣ ከአርሶ አደር እስከ አርብቶ አደር፣ ከነጋዴ እስከ መንግስት ሰራተኛ ያወጡት ገንዘብ ባክኖ እንዳልቀረ ማሳያ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ከሁሉም ኢትዮጵያውያን በተዋጣ ሀብት የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እንደተጠናቀቀ ሁሉ ሌሎች ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ለመጨረስ መረባረብ ይገባናል ብለዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም