ቀጥታ፡

በምክክር ሀገራዊ ችግሮችን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የበኩላችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል

ሆሳዕና ፤ ጥቅምት 11/2018(ኢዜአ) :- በምክክር ሀገራዊ ችግሮችን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የበኩላችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል ሲሉ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ። 

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀገሪቷ የሚስተዋሉ ዋና ዋና ችግሮችን በምክክር ለመፍታት ከተቋቋመ ጀምሮ እስካሁን በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።

ኮሚሽኑ ከዝግጅት ምዕራፍ በመጀመር በሁሉም አካባቢዎች በመንቀሳቀስ አሁን ላይ የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ እያካሄደ መሆኑ ይታወቃል።

በዚህ ሂደት የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ ሁሉን አቀፍና አካታች የውይይት ሂደትን አጠናክሮ የቀጠለ መሆኑንም ማረጋገጥ ይቻላል።

ከዚህ አንፃር በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የምክክር ሂደቱ የሀገርን ችግር በባለቤትነት በመያዝ በምክክር መፍታት የምንችልበት ታሪካዊ አጋጣሚ ላይ እንገኛለን ብለዋል። 

የኢትዮጵያን መሰረታዊ ችግሮች በውይይት ለመፍታት በሚደረገው ታሪካዊ አጋጣሚ የነቃ ትብብርና ተሳትፎ በማድረግ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የበኩላችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል ሲሉ አረጋግጠዋል።

በሀዲያና ስልጤ ሀገረ ስብከት የቁጥጥር መምሪያ ኃላፊና የሆሳዕና ደብረ መዊዕ ገዳም ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ መጋቢ ትፍስኢት ቀሲስ ዳዊት አብርሃም፤ ለችግሮች ሁሉ መፍቻ መንገድ ከውይይት የበለጠ አዋጭና አትራፊ መንገድ የለም ይላሉ።

በመሆኑም የሀገርን ችግሮች ተመካክሮ በመፍታት ለትውልዱ ሁሉ የተመቸችና ሰላም የሰፈነባት ሀገር ማጽናት የጋራ አደራና ሃላፊነታችን ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ጠንካራ ሀገረ መንግስትና ዜጎች ያለችግር የሚኖሩባት ሀገር ለመገንባት ያለ ልዩነት ለምክክር መሰባሰብ አለብን ሲሉም ተናግረዋል።

የአብሮነትንና የሰላም እሴቶችን ማጠናከር እንዲሁም ሰላምን ማስተማር የኃይማኖት አባቶች ዋነኛ ተልዕኮ መሆኑን አንስተው ለምክክሩ መሳካት የላቀ ሚናችንን ለመወጣት እንሰራለን ሲሉም አረጋግጠዋል።

የክልሉ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የወጣቶች ተወካይ እስማኤል ሻሜቦ፤ በበኩሉ በምክክር ሀገራዊ ችግሮችን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የበኩላችንን ለመወጣት እየሰራን እንገኛለን ይህንኑም አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።

በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ ችግሮችን በምክክር ለመፍታት ኮሚሽኑ የጀመራቸውን ስራዎች በማገዝ ረገድ በተለይም ቤተ እምነቶች ከፍተኛ ሃላፊነት ያለባቸው በመሆኑ በዚሁ ልክ ለማገዝ ተዘጋጅተናል ሲልም አረጋግጧል።

የቡታጅራ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ላቀች ወሰኔ፤ በሀገር ጉዳይ ላይ ተቀራርበን በመወያየት ችግሮችን መፍታት ባለመቻላችን ብዙ ዋጋ ያስከፈለን በመሆኑ አሁን ላይ ሁላችንም ለምክክር ዝግጁ መሆን አለብን ብለዋል።

በመሆኑም በምክክር ሂደቱ የነቃ ትብብርና ተሳትፎ በማድረግ ለሀገር ሰላም፣ ህብረ ብሔራዊ አንድነትና ለልማት እቅዶች ስኬት በጋራ መትጋት ይገባናል ሲሉ ተናግረዋል።

"እኛ ኢትዮጵያውያን በአብሮነት በመጓዝ ወደ ተሻለ ምዕራፍ እንድንደርስ የውስጥ ችግሮቻችንን በመነጋገርና በመወያየት የመፍታት ባህላችንን ማዳበር አለብን" ያሉት የኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማህበር ዋና ስራ አስፈፃሚ  ምህረት ተስፋዬ ናቸው፡፡

የጠመንጃ ትግል ኪሳራ እንጂ ትርፍ የሌለው በመሆኑ የሰላምን አማራጭ ብቻ በመከተል በምክክር ለችግሮች መፍትሄ ይዘን መቅረብ ይጠበቅብናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን "የሴቶች፣ የወጣቶችና የአካል ጉዳተኞች ሚናና አስተዋጽኦ ለውጤታማ ሀገራዊ ምክክር " በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ ክልሎች የውይይት መድረኮች በመካሄድ ላይ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም