ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሜጋ ፕሮጀክቶች የኢኮኖሚ እድገትን የሚያፋጥኑና ለአፍሪካውያን የመነሳት ምሳሌ ናቸው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 11/2018(ኢዜአ):- በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ ሜጋ የልማት ፕሮጀክቶች ኢኮኖሚያዊ እድገትን በማፋጠን የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ እና አፍሪካውያን በራሳቸው አቅም ግቦቻቸውን ለማሳካት የመነሳታቸው ማሳያ መሆናቸውን የምጣኔ ሀብት ምሁራን ገለጹ።

በኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማህበር የሰው ሃብት ልማትና ድህነት ቅነሳ ከፍተኛ ተመራማሪው ሞላ አለማየሁ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፥ ሀገራት ተግባራዊ የሚያደርጓቸው የልማት ሥራዎች እንደየነባራዊ ሁኔታቸው ቢለያዩም ጥቅል ግባቸው ሀገርን ወደ ከፍታ ማሻገር ነው።

በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት የዜጎቻቸውን ኑሮ የሚያሻሽሉና ኢኮኖሚያቸውን የሚያሳድጉ የልማት ሥራዎች ላይ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ጉልህ ፋይዳ አለው ብለዋል።

በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉና የተጠናቀቁ ሜጋ ፕሮጀክቶች በጥናት ላይ የተመሰረቱ፣ ዘላቂ ልማትን እና እድገትን በማሳካት የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋገጡ መሆናቸውን አብራርተዋል።

ለኢንቨስትመንት ተጨማሪ አቅምን መፍጠር የሚያስችሉ መሆናቸው ለአካታች ኢኮኖሚ ግንባታ መጎልበት ጉልህ ፋይዳ እንዳላቸውም ጠቁመዋል።

የኢኮኖሚ ልማት ባለሙያና የፋይናንስ ጉዳይ አማካሪ አቶ ደረጀ ደጀኔ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ፕሮጀክቶችን ጀምሮ የመጨረስ ባህል እየዳበረ መጥቷል ብለዋል።

የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ስራዎች፣ የከተሞችን ዕድገት የሚያፋጥኑና የዜጎችን ኑሮ የሚያሻሽሉ በርካታ መሰረተ ልማቶች መገንባታቸውንም በማሳያነት ጠቅሰዋል።

የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እድገት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግሩ ሜጋ ፕሮጀክቶች እየተጠናቀቁና እየተጀመሩ መሆናቸው ሀገራዊ ፋይዳቸው የላቀ መሆኑን አብራርተዋል።

እነዚሁ ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በኢንቨስትመንት ተመራጭና ተወዳዳሪ እንድትሆን ምቹ ሁኔታ መፍጠራቸውንም ነው ያስረዱት።

እንደ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ያሉ ፕሮጀክቶች ደግሞ ለጎረቤት ሀገራት የኃይል አቅርቦትን ጨምሮ በመሰረተ ልማት የመተሳሰር እድልን የሚፈጥሩ በመሆናቸው ለጋራ ዕድገት ወሳኝ ሚና አላቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሜጋ ፕሮጀክቶች ሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገትን ከማፋጠን ባለፈ አፍሪካውያን በራስ አቅም የትኛውንም የልማት ስራ በማከናወን ግቦቻቸውን ለማሳካት የመነሳታቸው ማሳያ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም