ቀጥታ፡

በምስራቅ ወለጋ ዞን በህብረተሰብ ተሳትፎ የወባ በሽታ ስርጭትን ለመከላከል ጥረት እየተደረገ ነው

ነቀምቴ፤ ጥቅምት 11/2018 (ኢዜአ)፡- የወባ በሽታን ስርጭትን በህብረተሰብ  ተሳትፎ  ለመከላከል ጥረት እየተደረገ መሆኑን የምስራቅ ወለጋ ዞን ጤና ፅህፈት ቤት ገለጸ።

የምስራቅ ወለጋ ዞን ጤና ፅህፈት ቤት ሀላፊ ቡልቶሳ ቡሻ እንደገለጹት የወባ በሽታ ስርጭትን ለመከላከል የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግና  የወባ ትንኝ መራቢያ ቦታዎችን ማፅዳት ስራ በትኩረት እየተከናወነ ይገኛል።

በእስካሁኑ ጥረትም የክረምት ወቅት መውጣቱን ተከትሎ የሚከሰትን የወባ ስርጭት ለመቆጣጠር ህብረተሰቡን ያሳተፈ ስራ ሲሰራ መቆየቱን ጠቁመዋል።

የወባ በሽታ ስርጭትን የመከላከል ስራውን ውጤታማ ለማድረግ በመረጃ ላይ የተመሰረተ የምርመራና የህክምና አገልግሎትን እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

የጤና ባለሙያዎች የቤት ለቤት ክትትል በማድረግ ህብረተሰቡ ጤናውን እንዲጠብቅ ግንዛቤ እየሰጡ ሲሆን  682 ሺህ 540 የአልጋ አጎበር መስራጨቱንና የኬሚካል ርጭት መካሄዱን አንስተዋል።

የነቀምቴ ከተማ ሶርጋ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሰኚ ሺፈራ፣ የወባ ወረርሽኝን ለመከላከል  በሚደረገው ጥረት ከሌሎች  ነዋሪዎች ጋር  በመተባበር  ውሀ ያቆሩ አካባቢዎችን  ማፋሰሳቸውን ተናግረዋል።

የጤና ባለሞያዎች በሚስተምሩዋቸው መሰረት የአልጋ  አጎበሮችን በአግባቡ  እየተጠቀሙ መሆኑን ገልጸው ወደ ፊትም የወባ በሽታ  ምልክት ሲያጋጥማችው ፈጥነው ወደ ህክምና ተቋም እንደሚሄዱም ተናግረዋል።

የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ምትኩ ግርማ በበኩላቸው በሽታውን ለመከላከልም የአካባቢ ጽዳት ላይ መስራታቸውን   አመልክተዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም