ዩኒቨርሲቲው የተሰጠውን ተልዕኮ ለመወጣት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲው የተሰጠውን ተልዕኮ ለመወጣት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሰራ ነው

ሮቤ፣ ጥቅምት11/2018(ኢዜአ) ፡-መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የተሰጠውን ተልዕኮ ለመወጣት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ብርሃነ መስቀል ጠና (ዶ/ር) ተናገሩ።
መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ በስፔን አገር ከሚገኘው ሰርጀሪ ሶሊዳሪቲ ከተባለ ድርጅት ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችለውን ስምምነት አድርጓል።
የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ብርሃነ መስቀል ጠና (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው የተሰጠውን ሀገራዊ ተልዕኮ ለመወጣት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሰራ ነው።
ዩኒቨርሲቲው በተለይ በጤና፣ በግብርና፣ በተፈጥሮ ሀብት፣ በቱሪዝምና በሌሎች ዘርፎች ላይ ልዩ ትኩረት በማድረግ እየሰራ መሆኑን አመልክቷል።
በተለይም በስሩ በሚገኘው የጎባ ሪፈራል ሆስፒታል የአካባቢው ማህበረሰብ የተሻለ የጤና አገልግሎት ማግኘት እንዲችል የተለያየ ጥረት እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
ከ”ሰርጀሪ ሶሊዳሪቲ” ድርጅት ጋር የተደረገው ስምምነትም በሆስፒታሉ እየተሰጠ የሚገኘውን የእንቅርት (ጎይተር) የቀዶ ህክምና አገልግሎትን በቴክኖሎጂ እንዲታገዝና ይበልጥ እንዲዘምን ዕድል እንደሚፈጥር አስረድተዋል።
በተጨማሪም ስምምነቱ በጎባ ሪፈራል ሆስፒታል የዘርፉ የህክምና ባለሙያዎች ዓለም አቀፍ ልምድ እንዲያገኙና የተሻለ የህክምናና የምርምር ስራዎችን በስፋት ለማካሄድ እንደሚረዳ ተናግረዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የጎባ ሪፈራል ሆስፒታል የእንቅርት የቀዶ ህክምና ማሻሻያ ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶክተር ከበበ በቀለ በበኩላቸው የተደረገው ስምምነት የእንቅርት ታማሚዎች የቀዶ ህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ከማድረግ ባሻገር የእውቀት ሽግግር ለማድረግ ያግዛል ብለዋል።
የድርጅቱ የሐኪሞች ቡድን በመጀመሪያ ቀን ውሎው ለአምስት የበሽታው ታካሚዎች የተሳካ የቀዶ ህክምና አገልግሎት ማድረጉንም አመልክተዋል።
በሚቀጥሉት አራት ቀናት በሆስፒታሉ ቀድመው የተለዩ ሌሎች 25 ታካሚዎች የህክምና አገልግሎት ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ጠቁመዋል።
የ”ሰርጀሪ ሶሊዳሪቲ” ድርጅት ሊቀመንበር ዶክተር ጆሴ ማኑኤል በበኩላቸው፤ በሁለቱ ተቋማት መካከል የተደረገው የመግባቢያ ስምምነት በተለይ በእንቅርት የቀዶ ህክምና ዘርፍ የእውቀት ሽግግር ለማድረግ ዕድልን እንደሚፈጥር ገልጸዋል።