ቀጥታ፡

ባለሀብቶች በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ኢንቨስትመንት ዘርፍ ላይ ለመሰማራት ከፍተኛ ፍላጎት እያሳዩ ነው

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 11/2018(ኢዜአ):-የውጭ እና የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ማምረትና መገጣጠም ዘርፍ ለመሰማራት ከፍተኛ ፍላጎት እያሳዩ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በርኦ ሀሰን ገለጹ።  

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ማስፋፋት የአየር ብክለትን እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ትልቅ አስተዋፅኦ አለው።

ከኢኮኖሚ ጥቅሞች መካከልም የነዳጅ እና የጥገና ወጪን በመቀነስ፣ የውጭ ምንዛሪን በመቆጠብ እንዲሁም ለባትሪ፣ ለኃይል መሙያ ጣቢያዎች እና ለመገጣጠሚያ ዘርፍ አዲስ የሥራ እና የኢንቨስትመንት ዕድሎችን ይፈጥራል። 


 

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በርኦ ሀሰን እንዳሉትም፤ ኢትዮጵያ በመጪዎቹ አስር ዓመታት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ቁጥር ከ500 ሺህ በላይ ለማድረስ ዕቅድ ይዛ እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከውጭ የሚገቡ ተሽከርካሪዎችን 99 በመቶ ኤሌክትሪክ የማድረግ ዕቅዱም ተግባራዊ መደረግ መጀመሩን ጠቅሰው፤ አሁን ላይ ካሉት አጠቃላይ ተሽከርካሪዎች ውስጥ ሰባት በመቶው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል። 

መንግሥት ለዘርፉ መጠናከር ትልቅ ትኩረት መስጠቱን አንስተው፤ የመንግሥት ግዢ ሙሉ በሙሉ ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች መዞሩ የግሉ ዘርፍ የመንግሥትን ፈለግ እንዲከተል የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።  

መንግስት የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎችን ለማስፋፋት የተለያዩ ማበረታቻዎችን ማድረጉን ጠቁመው፤ ውሳኔዎቹ የዘርፉን መነቃቃት ይበልጥ የሚያጎሉ ናቸው ብለዋል፡፡ 


 

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች አረንጓዴ ታርጋ እንዲኖራቸው ልዩ ልዩ ማበረታቻዎች እንደሚደረጉላቸውም አስታውቀዋል።

ከውጭ ባለሀብቶች በተለይም ከቼክ ሪፐብሊክ፣ ጀርመን፣ ኖርዌይ እና ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት እንዲሁም ከሀገር ውስጥ በርካታ ኢንቨስተሮች በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ማምረት እና መገጣጠም ላይ ለመሰማራት ጥያቄዎችን ማቅረባቸውን ጠቅሰዋል፡፡ 

መንግሥት የኢንቨስትመንት ጥያቄዎች ተቀብሎ ለማስፈጸም የሚያስችል አስፈላጊ ስትራቴጂ መዘርጋቱን ጠቁመዋል፡፡ 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም