ቀጥታ፡

የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር መመሪያ የፍትህ መጓተትን በማስቀረት ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውቷል

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 11/2018(ኢዜአ):-የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር መመሪያ የፍትህ መጓተትን በማስቀረት ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውቷል ሲሉ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ፉአድ ኪያር ገለጹ።

የጉዳዮች ‎ፍሰት አስተዳዳር የዳኝነት አገልግሎት ቀልጣፋ፣ ተገማችና ተገልጋይ እርካታ የሚያገኝበት እንዲሆን ከማድረጉ ባሻገር የአገልግሎት ጥራትን ለማሳደግና፤ የመዝገብ ክምችትን ለመቀነስ ጉልህ ድርሻ አለው፡፡

የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር የጉዳዮች መቋጫና እልባት መስጫ ጊዜ መጓተት የሚያስከትለውን ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ መቀነስ የሚያስችል የአሰራር ስርዓት ለመዘርጋት ወሳኝ መሆኑን ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ 

እንዲሁም የዳኝነት ነፃነት፣ ተጠያቂነትና ሚዛናዊነት ተጠብቆ ዜጎች በአጭር ጊዜ ጥራት ያለው የዳኝነት አገልግሎት እንዲያገኙና በዳኝነት ስርዓቱ ላይ ያላቸው አመኔታና እርካታ እያደገ እንዲሄድ የሚያስችል ነው፡፡

የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ፉአድ ኪያር ለኢዜአ እንደገለጹት ከለውጡ በኋላ በፍትህ ዘርፉ የተደረጉ ዋና ዋና ሪፎርሞች ውጤት በማስገኘት ላይ ናቸው ።

‎በተለይም ለፍትህ እጦት በምክንያትነት ሲጠቀስ የነበረውን የጉዳዮች መጓተት ለማስቀረት ከለውጡ በኋላ ከተወሰዱት መጠነ ሰፊ እርምጃዎች መካከል የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር ትልቅ ቦታ እንደሚሰጠው ገልጸዋል።

‎ፕሬዝዳንቱ እንደገለጹት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በ2014 ዓ.ም. ያወጣው የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር መመሪያ  የጉዳዮች መጓተትን ከመቅረፍ አንጻር  ቁልፍ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

‎‎ቀደም ሲል አንድ ጉዳይ የሚጀመርበትና የሚያልፍበት የጊዜ ገደብ እንደማይታወቅ አስታውሰው፣ አሁን ባለው መመሪያ ግን ለእያንዳንዱ ጉዳይ ግልጽ የጊዜ ገደብ ተቀምጦ እየተሰራበት ይገኛል ብለዋል።

‎በአሁኑ ወቅት የጊዜ ገደብ ያለፈባቸው ፋይሎች ላይ የዘገየ የሚል ምልክት በመለጠፍና ለጉዳዩ ቅድሚያ በመስጠት የተቀላጠፈ  ውሳኔ እንዲሰጥባቸው እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

‎ከዚህ ባለፈ ያለአግባብ ቀጠሮ በሚያዛቡ ዳኞች ላይ ተጠያቂነት የማስፈን ስራ መጀመሩን ጠቁመው፤ ይህም ዳኞች ጉዳዮችን በፍጥነት እንዲያዩ በማድረግ፣ የጉዳዮች መዘግየት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ አድርጓል ብለዋል።

‎ከሪፎርሙ በኋላ በፍርድ ቤት አገልግሎት ተደራሽነትና በዳኝነት ነጻነት ላይ ከፍተኛ ለውጥ መታየቱን ፕሬዝዳንቱ አመልክተዋል። 

በፍትህ ስርዓቱ አሰራር ላይ ተግባራዊ መደረግ የጀመረው የቴክኖሎጂ ስራ መልካም አስተዳደርን ለማረጋገጥና ቀልጣፋ ውሳኔ ለመስጠት አስቻይ ሁኔታ መፍጠሩን ፕሬዝዳንቱ ጨምረው ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም