በአማራ ክልል የገጠር ኮሪደር ልማትን በመተግበር የአርሶ አደሩን የአኗኗር ዘይቤ ለመለወጥ ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የገጠር ኮሪደር ልማትን በመተግበር የአርሶ አደሩን የአኗኗር ዘይቤ ለመለወጥ ትኩረት ተሰጥቷል
ደብረ ብርሃን ፤ ጥቅምት 11/2018(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል የገጠር ኮሪደር ልማትን በመተግበር የአርሶ አደሩን የአኗኗር፣ የአመራረትና የአሰራር ዘይቤ ለመለወጥ ትኩረት መሰጠቱን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) ገለጹ።
በገጠር ኮሪደር ልማት አተገባበር ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ ዛሬ በደብረ ብርሃን ከተማ ተካሄዷል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ በገጠር የሚኖረውን ማሕበረሰብ አኗኗርና አሰራር ማዘመን ወቅቱ የሚጠይቀው ተግባር ነው።
ለዚህም በዲጂታላይዜሽን የታገዘ የመሰረተ ልማት፣ የቤት ግንባታና ቀልጣፋና ፍትሃዊ የመንግስት አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ አንስተዋል።
ይህንን እውን ለማድረግ የገጠር ኮሪደር ልማትን ፈጥኖ ወደ መተግበር በመሸጋገር የገጠሩን አካባቢ ለኢንቨስትመንት፣ ለኑሮና ለጎብኚዎች ተመራጭ ለማድረግ ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።
የአርሶ አደሩን የኑሮ ሁኔታ በማሻሻል የግብርናውን ምርታማነት ለማሳደግ፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ለማሻሻልና ገጠሩን የእድገት ማዕከል ለማድረግ ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።
የገጠር ኮሪደር ልማትን ተግባራዊ ለሚያደርጉ አካባቢዎችም የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት በበኩላቸው እንደገለጹት፤ በደብረ ብርሃን በሚገኙ አምስት ክፍለ ከተሞች በተመረጡ የገጠር ቀበሌዎች የገጠር ኮሪደር ልማት ዘንድሮ ይተገበራል።
እስካሁን በተደረገው እንቅስቃሴም የኮሪደር ልማቱ የሚተገበርባቸውን ቀበሌዎች የመለየትና ሕብረተሰቡን በማወያየት የጋራ መግባባት መፍጠር መቻሉን አስታውቀዋል።
በቀጣይም ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ያሉ አቅሞችን አሟጦ በመጠቀም የኮሪደር ልማቱን ለማሳካት ጥብቅ አመራር በመስጠት እንደሚተገበር ተናግረዋል።
ከጠባሴ ክፍለ ከተማ የአንጎለላ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ከፈለኝ ተሾመ በሰጡት አስተያየት፤ የገጠር ኮሪደር ልማት መምጣቱ የአርሶ አደሩን አኗኗር በመቀየር የተሻለ ህይወት እንዲኖር የሚያስችል ነው ብለዋል።
በመሆኑም ካላቸው ሃብትና ጉልበት በማዋጣት የገጠር ኮሪደር ልማቱን ለማካሄድ የበኩላቸውን ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
በከተማው ሲካሄድ የቆየው የኮሪደር ልማትን ሲመለከቱ ቁጭት እንዳደረባቸው የተናገሩት ደግሞ ከጫጫ ክፍለ ከተማ የመጡት አቶ ተክሉ ሀብተወልድ ናቸው።
አሁን ላይ ወደ ገጠሩ በመምጣቱ አካባቢያችንን ውብና ማራኪ በማድረግ አኗኗራችን እንዲዘምን የበኩሌን ለመወጣት ዝግጁ ነኝ ብለዋል።