ቀጥታ፡

በአማራ ክልል ሰላምን በማጽናት በሁሉም መስኮች የተከናወኑ የልማት ስራዎች የህዝብን ተጠቃሚነት መሰረት ያደረጉ ናቸው

ጎንደር ፤ ጥቅምት 11/2018 (ኢዜአ)፡  በአማራ ክልል ሰላምን በማጽናት በሁሉም መስኮች የተከናወኑ የልማት ስራዎች የህዝብን ተጠቃሚነት መሰረት ያደረጉ መሆናቸውን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ሃላፊ አሕመዲን መሐመድ (ዶ/ር) ገለጹ። 

የጎንደር ከተማ አስተዳደር የበጀት ዓመቱ ሶሰት ወራት የፓርቲ እና የመንግሥት የስራ አፈጻጸም የግምገማ መድረክ በመካሄድ ላይ ይገኛል።


 

በመድረኩ ላይ የተገኙት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ  አህመዲን ሙሐመድ (ዶ/ር)፤ በአማራ ክልል ሰላምን በማጽናት በሁሉም መስኮች የተከናወኑ የልማት ስራዎች የህዝብን ተጠቃሚነት መሰረት ያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከዚህ አንፃር በጎንደር ከተማ የተከናወኑ የመሰረተ ልማትና የፕሮጀክቶች ግንባታዎች ጥሩ አፈፃፀም የታየባቸው መሆኑን አንስተው የመንግሥት ተቋማትን የአገልግሎት አሰጣጥ ምቹ እና የተቀላጠፈ በማድረግ የህዝብን እንግልት ለማስቀረት የተከናወኑ ተግባራትም የሚበረታቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በጎንደር ከተማም እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎች ፈጠራን፣ የፍጥነትን፣ ጥራትና አዲስ የስራ ባህል ለውጥን በማምጣት አበረታች ውጤት የታየባቸው መሆናቸውን ገልጸዋል።

በኮሪደር ልማት፣ በቅርስ ጥገናና እድሳት፣ በስራ እድል ፈጠራና ሌሎች የመሰረተ ልማት ግንባታዎች የተመዘገቡት ውጤቶች ሰላምን በጋራ በማረጋገጥ የመጣ ውጤት መሆኑን አስረድተዋል።

እንደ አጠቃላይ የክልሉ መንግስት የቀጣይ 25 ዓመት አሻጋሪ የልማት እቅድ ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀቱንም ዶክተር አሕመዲን ጠቁመዋል። 

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው፤ በከተማ አስተዳደሩ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ሰላምን በማስጠበቅ የተከናወኑ የልማትና  የመልካም አስተዳደር ስራዎች በውጤት የተለኩና የህዝቡንም እርካታ በተጨባጭ ያረጋገጡ ናቸው ብለዋል።    


 

የዛሬ መድረክም የተሳኩ እቅዶችን የምናጠናክርበት፣ ደካማ አፈጻጸሞችን የምናርምበትና በቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ መግባባት በመፍጠር የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ የምንተጋበት ነው ሲሉ ገልጸዋል።    

በመድረኩ የክልሉና  በየደረጃው የሚገኙ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም